ምዕራፍ 43

፤ራብም በምድር ጸና።
2 ፤ ከግብፅም ያመጡትን እህል በልተው ከፈጸሙ በኋላ አባታቸው። እንደ ገና ሂዱ፤ ጥቂት እህል ሸምቱልን አላቸው።
3 ፤ ይሁዳም እንዲህ አለው። ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎ በብርቱ ቃል አስጠነቀቀን።
4 ፤ ወንድማችንን ከእኛ ጋር ብትሰድደው እንወርዳለን፥ እህልም እንሸምትልሃለን፤
5 ፤ ባትሰድደው ግን አንሄድም፤ ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎናልና።
6 ፤ እስራኤልም አላቸው። ለምን በደላችሁኝ? ለዚያውስ። ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለምን ነገራችሁት?
7 ፤ እነርሱም አሉ። ያ ሰው ስለ እኛና ስለ ወገናችን ፈጽሞ ጠየቀን እንዲህም አለን። አባታችሁ ገና በሕይወት ነው? ወንድምስ አላችሁን? እኛም እንደዚሁ እንደ ጥያቄው መለስንለት፤ በውኑ። ወንድማችሁን አምጡ እንዲለን እናውቅ ነበርነን?
8 ፤ ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው። እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ስደደው፥ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን።
9 ፤ እኔ ስለ እርሱ እዋሳለሁ ከእጄ ትሻዋለህ፤ ወደ አንተ ባላመጣው፥ በፊትህም ባላቆመው፥ በዘመናት ሁሉ አንተን የበደልሁ ልሁን።
10 ፤ ባንዘገይስ ኖሮ አሁን ሁለተኛ ጊዜ በተመለስን ነበር።
11 ፤ እስራኤልም አባታቸው እንዲህ አላቸው። ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህንን አድርጉ፤ ከተመሰገነው ከምድሩ ፍሬ በዓይበታችሁ ይዛችሁ ሂዱ፥ ለዚያም ሰው እጅ መንሻ፥ ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ከርቤ፥ ተምር፥ ለውዝ ውሰዱ።
12 ፤ ብሩን በአጠፌታ አድርጋችሁ በእጃችሁ ውሰዱ፤ በዓይበታችሁ አፍ የተመለሰውንም ብር መልሳችሁ ውሰዱ፤ ምናልባት በስሕተት ይሆናል።
13 ፤ ወንድማችሁንም ውሰዱ፥ ተነሥታችሁም ወደዚያ ሰው ተመለሱ።
14 ፤ ሁሉን የሚችል አምላክም ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ከእናንተ ጋር ይሰድድ ዘንድ በዚያ ሰው ፊት ምሕረትን ይስጣችሁ፤ እኔም ልጆቼን እንዳጣሁ አጣሁ።
15 ፤ ሰዎቹም በእጃቸው ያችን እጅ መንሻና አጠፌታውን ብር ብንያምንም ወሰዱ፤ ተነሥተውም ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በዮሴፍም ፊት ቆሙ።
16 ፤ ዮሴፍም ብንያምን ከእነርሱ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው። እነዚያን ሰዎች ወደ ቤት አስገባቸው፥ እርድም እረድ አዘጋጅም፥ እነዚያ ሰዎች በእኩለ ቀን ከእኔ ጋር ይበላሉና።
17 ፤ ያ ሰውም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤ ያ ሰውም ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባ።
18 ፤ እነርሱም ወደ ዮሴፍ ቤት ስለ ገቡ ፈሩ፤ እንዲህም አሉ። በዓይበታችን ቀድሞ ስለ ተመለሰው ብር ሊተነኰልብን ሊወድቅብንም፥ እኛንም በባርነት ሊገዛ አህዮቻችንንም ሊወስድ ወደዚህ አስገባን።
19 ፤ ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥም ቀረቡ፥ በቤቱም ደጅ ተናገሩት፥
20 ፤ እንዲህም አሉት። ጌታዬ ሆይ፥ ቀድሞ እህልን ልንሸምት ወርደን ነበር፤
21 ፤ ወደምናድርበትም ስፍራ በደረስን ጊዜ ዓይበታችንን ከፈትን፥ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ብር በየዓይበቱ አፍ እንደ ሚዛኑ ብራችን ነበረ፤ አሁንም በእጃችን መለስነው።
22 ፤ እህል እንሸምትበት ዘንድ ሌላም ብር በእጃችን አመጣን፤ ብራችንንም በዓይበታችን ማን እንደ ጨመረው አናውቅም።
23 ፤ እርሱም አላቸው። ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ አትፍሩ፤ አምላካችሁና የአባታችሁ አምላክ በዓይበታችሁ የተሰወረ ገንዘብ ሰጣችሁ፤ ብራችሁስ ደርሶኛል።
24 ፤ ስምዖንንም አወጣላቸው። ሰውዮውም እነዚያን ስዎች ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸው፤ ውኃ አመጣላቸው፥ እግራቸውንም ታጠቡ፤ ለአህዮቻቸው አበቅ ሰጣቸው።
25 ፤ ዮሴፍም በእኩለ ቀን እስኪገባ ድረስ እነርሱ እጅ መንሻቸውን አዘጋጁ፥ ከዚያ እንጀራን እንደሚበሉ ሰምተዋልና።
26 ፤ ዮሴፍም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ በእጃቸው ያለውን እጅ መንሻ በቤት ውስጥ አቀረቡለት፥ ወደ ምድርም ወድቀው ሰገዱለት።
27 ፤ እርሱም ደኅንነታቸውን ጠየቃቸው፥ እንዲህም አለ። የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ ደኅና ነውን? ገና በሕይወት አለን?
28 ፤ እነርሱም አሉት። ባሪያህ አባታችን ደኅና ነው፤ ገና በሕይወት አለ። አጐንብሰውም ሰገዱለት።
29 ፤ ዓይኑንም አንሥቶ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየው፥ እርሱም አለ። የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነውን? እንዲህም አለው። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ።
30 ፤ ዮሴፍም ቸኮለ፥ አንጀቱ ወንድሙን ናፍቆታልና፤ ሊያለቅስም ወደደ፤ ወደ እልፍኙም ገብቶ ከዚያ አለቀሰ።
31 ፤ ፊቱንም ታጥቦ ወጣ፥ ልቡንም አስታግሦ። እንጀራ አቅርቡ አለ።
32 ፤ ለእርሱም ለብቻው አቀረቡ፥ ለእነርሱም ለብቻቸው፥ ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ለግብፅ ሰዎችም ለብቻቸው፤ የግብፅ ሰዎች ከዕብራውያን ጋር መብላት አይሆንላቸውምና፥ ይህ ለግብፅ ሰዎች እንደ መርከስ ነውና።
33 ፤ በፊቱም በኵሩ እንደ ታላቅነቱ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ ተቀመጡ፤ ሰዎቹም እርስ በርሳቸው ተደነቁ።
34 ፤ በፊቱም ካለው መብል ፈንታቸውን አቀረበላቸው፤ የብንያምም ፈንታ ከሁሉ አምስት እጅ የሚበልጥ ነበረ። እነርሱም ጠጡ ከእርሱም ጋር ደስ አላቸው።