ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 38
በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ፥ ስሙን ኤራስ ወደሚሉት ወደ ዓዶሎማዊውም ሰው ገባ።
2 ፤ ከዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ ወሰዳትም፥ ወደ እርስዋም ገባ።
3 ፤ ፀነሰችም ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው።
4 ፤ ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው።
5 ፤ እንደ ገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች፥ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፤ እርሱንም በወለደች ጊዜ ክዚብ በሚባል አገር ነበረች።
6 ፤ ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔር ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው።
7 ፤ የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው።
8 ፤ ይሁዳም አውናን። ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፥ አግባትም፥ ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው።
9 ፤ አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስስው ነበር።
10 ፤ ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው።
11 ፤ ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን። ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች።
12 ፤ ከብዙ ዘመንም በኋላ የይሁዳ ሚስት የሴዋ ልጅ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፥ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፥ እርሱም ዓዶሎማዊው ወዳጁም ኤራስ።
13 ፤ ለትዕማርም። እነሆ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል ብለው ነገሩአት።
14 ፤ እርስዋም የመበለትነትዋን ልብስ አወለቀች፥ መጎናጸፊያዋንም ወሰደች፥ ተሸፈነችም፥ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ ሚስትም እንዳልሆነችው አይታለችና።
15 ፤ ይሁዳም ባያት ጊዜ ጋለሞታን መሰለችው፤ ፊትዋን ተሸፍና ነበርና።
16 ፤ ወደ እርስዋም አዘነበለ። እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤ እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም። ወደኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ? አለችው።
17 ፤ የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት። እርስዋም። እስክትሰድድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህን? አለችው።
18 ፤ እርሱም። ምን መያዣ ልስጥሽ? አላት። እርስዋም። ቀለበትህን፥ አምባርህን፥ በእጅህ ያለውን በትር አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ጋር ደረሰ፥ እርስዋም ፀነሰችለት።
19 ፤ እርስዋም ተነሥታ ሄደች፥ መጎናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነትዋን ልብስ ለበሰች።
20 ፤ ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በወዳጁ በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት፤ እርስዋንም አላገኛትም።
21 ፤ እርሱም የአገሩን ሰዎች። በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ጋለሞታ ወዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። በዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉት።
22 ፤ ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው። አላገኘኋትም፤ የአገሩም ሰዎች ደግሞ። ከዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉኝ።
23 ፤ ይሁዳም። እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው፤ እነሆ የፍየሉን ጠቦት ሰደድሁላት፥ አንተም አላገኘሃትም አለ።
24 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ። ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ ደግሞም በዝሙት እነሆ ፀነሰች ብለው ነገሩት። ይሁዳም። አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ።
25 ፤ እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች። ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት፤ ተመልከት፤ ይህ ቀለበት፥ ይህ አምባር፥ ይህ በትር የማን ነው?
26 ፤ ይሁዳም አወቀ። ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና አለ። ደግሞም አላወቃትም።
27 ፤ በመውለጃዋም ጊዜ እነሆ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ።
28 ፤ ስትወልድም አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች። ይህ መጀመሪያ ይወጣል አለች።
29 ፤ እንዲህም ሆነ፤ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም። ለምን ጥስህ ወጣህ? አለች፤ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው።
30 ፤ ከእርሱም በኋላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ ተባለ።