ምዕራፍ 33

ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ፥ እነሆም ዔሳውን ሲመጣ አየው፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም ባሪያዎች አደረጋቸው፤
2 ፤ ባሪያዎችንና ልጆቻቸውንም በፊት አደረገ፥ ልያንና ልጆችዋንም በኋለኛው ስፍራ፥ ራሔልንና ዮሴፍንም ከሁሉ በኋላ አደረገ።
3 ፤ እርሱም በፊታቸው አለፈ፤ ወደ ወንድሙም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ።
4 ፤ ዔሳውም ሊገናኘው ሮጠ፥ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፤ ተላቀሱም።
5 ፤ ዓይኑንም አነሣና ሴቶችንና ልጆችን አየ፥ እንዲህም አለ። እነዚህ ምኖችህ ናቸው? እርሱም። እግዚአብሔር ለእኔ ለባሪያህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው አለ።
6 ፤ ሴቶች ባሪያዎችም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው ሰገዱ፤
7 ፤ ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀርበው ሰገዱ፤ ከዚያም በኋላ ዮሴፍና ራሔል ቀርበው ሰገዱ።
8 ፤ እርሱም። ያገኘሁት ይህ ሠራዊት ሁሉ ምንህ ነው? አለ። እርሱም። በጌታዬ ፊት ሞገስን አገኝ ዘንድ ነው አለ።
9 ፤ ዔሳውም። ለእኔ ብዙ አለኝ፤ ወንድሜ ሆይ፥ የአንተ ለአንተ ይሁን አለ።
10 ፤ ያዕቆብም አለ። እንደዚህ አይደለም፤ ነገር ግን በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅ መንሻዬን ተቀበለኝ፤ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቼአለሁና፥ በቸርነትም ተቀብለኸኛልና።
11 ፤ ይህችንም ያመጣሁልህን በረከቴን ተቀበል፤ እግዚአብሔር በቸርነት ሰጥቶኛልና፥ ለእኔም ብዙ አለኝና። እስኪቀበለውም ድረስ ዘበዘበው።
12 ፤ እርሱም። ተነሣና እንሂድ፥ እኔም በፊትህ እሄዳለሁ አለ።
13 ፤ እርሱም አለው። ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ።
14 ፤ ጌታዬ ከባሪያው ፊት ቀድሞ ይለፍ፤ እኔም ወደ ሴይር ከጌታዬ ዘንድ እስክደርስ ድረስ ከፊቴ ባሉት በእንስሳቱ እርምጃና በሕፃናቱ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ።
15 ፤ ዔሳውም። ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች ከፍዬ ልተውልህን? አለ። እርሱም። ይህ ለምንድር ነው? በጌታዬ ዘንድ ሞገስን ማግኘት ይበቃኛል አለ።
16 ፤ ዔሳውም በዚያን ቀን ወደ ሴይር መንገዱን ተመለሰ።
17 ፤ ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ በዚያም ለእርሱ ቤትን ሠራ፥ ለከብቶችም ዳሶችን አደረገ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ሱኮት ብሎ ጠራው።
18 ፤ ያዕቆብም ከሁለት ወንዞች መካከል በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም ከተማ በደኅንነት መጣ፤ በከተማይቱም ፊት ሰፈረ።
19 ፤ ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውንም የእርሻውን ክፍል ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛው።
20 ፤ በዚያም መሠውያውን አቆመ፥ ያንም ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።