ምዕራፍ 12

እግዚአብሔርም አብራምን አለው። ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።
2 ፤ ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤
3 ፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።
4 ፤ አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።
5 ፤ አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ።
6 ፤ አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ሞሬ የአድባር ዛፍ ድረስ በምድር አለፈ፤ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድሩ ነበሩ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና። ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ።
8 ፤ ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፥ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ።
9 ፤ አብራምም ከዚያ ተነሣ፥ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ።
10 ፤ በምድርም ራብ ሆነ፤ አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፥ በምድር ራብ ጸንቶ ነበርና።
11 ፤ ወደ ግብፅም ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት። አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ
12 ፤ የግብፅ ሰዎች ያዩሽ እንደ ሆነ። ሚስቱ ናት ይላሉ እኔንም ይገድሉኛል፥ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል።
13 ፤ እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፥ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ። እኅቱ ነኝ በዪ።
14 ፤ አብራምም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የግብፅ ሰዎች ሴቲቱን እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፤
15 ፤ የፈርዖንም አለቆች አዩአት፥ በፈርዖንም ፊት አመሰገኑአት፤ ሴቲቱንም ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱአት።
16 ፤ ለአብራምም ስለ እርስዋ መልካም አደረገለት፤ ለእርሱ በጎችም በሬዎችም አህዮችም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም ግመሎችም ነበሩት።
17 ፤ እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ።
18 ፤ ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብኝ ምንድር ነው? እርስዋ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም?
19 ፤ ለምንስ። እኅቴ ናት አልህ? እኔ ሚስት ላደርጋት ወስጄአት ነበር። አሁንም ሚስትህ እነኋት፤ ይዘሃት ሂድ።
20 ፤ ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ እርሱ አዘዘ፥ እርሱንም ሚስቱንም ከብቱንም ሁሉ ሸኙአቸው።