ምዕራፍ 23

የሣራም ዕድሜ መቶ ሀያ ሰባት ዓመት ሆነ።
2 ፤ በቂርያትአርባቅም ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ።
3 ፤ አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ፥
4 ፤ ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ። እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፤ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ርስት ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ ልቅበር።
5 ፤ የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፥ አሉትም።
6 ፤ ጌታ ሆይ፥ ስማን፤ አንተ በእኛ መካከል ከእግዚአብሔር አለቃ ነህ፤ ከመቃብር ስፍራችን በመልካሙ ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም።
7 ፤ አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም፥ ለኬጢ ልጆች፥ ሰገደ።
8 ፤ እንዲህም አላቸው። ሬሳዬን ከፊቴ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፥ ከሰዓር ልጅ ከኤፍሮንም ለምኑልኝ፤
9 ፤ በእርሻው ዳር ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን በሙሉ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፥ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን።
10 ፤ ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።
11 ፤ አይደለም፥ ጌታዬ፥ ስማኝ፤ እርሻውን ሰጥቼሃለሁ በእርሱም ዳር ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር።
12 ፤ አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤
13 ፤ የአገሩ ሰዎችም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ። ነገሬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የእርሻውን ዋጋ እሰጥሃለሁ፤ አንተም ከእኔ ዘንድ ውሰድ፥ ሬሳዬንም በዚያ እቀብራለሁ።
14 ፤ ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።
15 ፤ ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፤ የአራት መቶ ሰቅል ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካክለ ምንድር ነው? ሬሳህንም ቅበር።
16 ፤ አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ፤ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውን አራት መቶ ሰቅል መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው፤ ብሩም ለመሸጫ ለመለወጫ የሚተላለፍ ነበረ።
17 ፤ በመምሬ ፊት ያለው ባለድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻ ለአብርሃም ጸና፤
18 ፤ እርሻው በእርሱም ያለው ዋሻው፥ በእርሻውም ውስጥ በዙሪያውም ያለው እንጨት ሁሉ በኬጢ ልጆችና በከተማይቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ።
19 ፤ ከዚህም በኋላ ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን ቀበረ።
20 ፤ እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻው በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና።