ምዕራፍ 16

የአብራም ሚስት ሦራ ግን ለአብራም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት ባሪያም ነበረቻት።
2 ፤ ሦራም አብራምን። እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፤ ምናልባት ከእርስዋ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርስዋ ግባ አለችው።
3 ፤ አብራምም የሦራን ቃል ሰማ። አብራምም በከነዓን ምድር አሥር ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባሪያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው።
4 ፤ እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች።
5 ፤ ሦራም አብራምን። መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ አለችው።
6 ፤ አብራምም ሦራን። እነሆ ባሪያሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦራም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች።
7 ፤ የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው።
8 ፤ እርሱም። የሦራ ባሪያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ? አላት። እርስዋም። እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ አለች።
9 ፤ የእግዚአብሔር መልአክም። ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ አላት።
10 ፤ የእግዚአብሔር መልአክም። ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት።
11 ፤ የእግዚአብሔር መልአክም አላት። እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና።
12 ፤ እርሱም የበዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል፤ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፥ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል።
13 ፤ እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና።
14 ፤ ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው።
15 ፤ አጋርም ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው።
16 ፤ አጋር እስማኤልን ለአብራም በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ ስድስት ዓመት ሰው ነበረ።