ምዕራፍ 4

አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም። ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች።
2 ፤ ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ።
3 ፤ ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤
4 ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤
5 ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ?
7 ፤ መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት።
8 ፤ ቃየንም ወንድሙን አቤልን። ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።
9 ፤ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ። አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?
10 ፤ አለውም። ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል።
11 ፤ አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።
12 ፤ ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።
13 ፤ ቃየንም እግዚአብሔርን አለው። ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት።
14 ፤ እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።
15 ፤ እግዚአብሔርም እርሱን አለው። እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት።
16 ፤ ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።
17 ፤ ቃየንም ሚስቱን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፥ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሄኖሕ አላት።
18 ፤ ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሣኤልን ወለደ፤ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ።
19 ፤ ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበረ።
20 ፤ ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ።
21 ፤ የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ።
22 ፤ ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች።
23 ፤ ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው። እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፥ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጕልማሳውን ለቍስሌ፥ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና፤
24 ፤ ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ። ይበቀሉታል
25 ፤ አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም። ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው።
26 ፤ ለሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ።