ምዕራፍ 17

አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና። እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤
2 ፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው።
3 ፤ አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው። እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፤
4 ፤ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ።
5 ፤ ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና።
6 ፤ እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ።
7 ፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ።
8 ፤ በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር፥ የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ።
9 ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፥ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው።
10 ፤ በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ።
11 ፤ የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል።
12 ፤ የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ።
13 ፤ በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል።
14 ፤ የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቈላፍ ሰው ሁሉ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፤ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።
15 ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ።
16 ፤ እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርስዋ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ።
17 ፤ አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ። የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን?
18 ፤ አብርሃምም እግዚአብሔርን። እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር አለው።
19 ፤ እግዚአብሔርም አለ። በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ።
20 ፤ ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ።
21 ፤ ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ።
22 ፤ ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ።
23 ፤ አብርሃምም ልጁን እስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ፥ በብሩም የገዛቸውን ሁሉ፥ ከአብርሃም ቤተ ሰብ ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ፥ የቍልፈታቸውንም ሥጋ እግዚአብሔር እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ።
24 ፤ አብርሃምም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበረ፤
25 ፤ ልጁ እስማኤልም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበረ።
26 ፤ በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ፥ ልጁ እስማኤልም።
27 ፤ በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት የቤቱ ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ።