ምዕራፍ 41

ከሁለት ዓመት በኋላም ፈርዖን ሕልምን አየ፥ እነሆም፥ በወንዙ ዳር ቆሞ ነበር።
2 ፤ እነሆም፥ መልካቸው ያማረ ሥጋቸውም የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፥ በውኃውም ዳር በመስኩ ይሰማሩ ነበር።
3 ፤ ከእነርሱም በኋላ እነሆ መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዝ ወጡ፥ በእነዚያም ላሞች አጠገብ በወንዙ ዳር ይቆሙ ነበር።
4 ፤ መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ እነዚያም ላሞች መልካቸው ያማረውን ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ።
5 ፤ ደግሞም ተኛ ሁለተኛም ሕልምን አየ። እነሆም በአንድ አገዳ ላይ የነበሩ ያማሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች ወጡ፤
6 ፤ እነሆም ከእነርሱ በኋላ የሰለቱና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤
7 ፤ የሰለቱትም እሸቶች ሰባቱን ያማሩና የዳበሩ እሸቶች ዋጡአቸው።
8 ፤ ፈርዖንም ነቃ፥ እነሆም ሕልም ነበረ። በነጋም ጊዜ ነፍሱ ታወከችበት፤ ወደ ሕልም ተርጓሚዎች ሁሉ ወደ ግብፅ ጠቢባንም ሁሉ ልኮ ወደ እርሱ ጠራቸው፤ ፈርዖንም ሕልሙን ነገራቸው፥ ነገር ግን ከእነርሱ ለፈርዖን የሚተረጕም አልተገኘም።
9 ፤ የዚያን ጊዜ የጠጅ አሳላፈዎቹ አለቃ እንዲህ ብሎ ለፈርዖን ተናገረ። እኔ ኃጢአቴን ዛሬ አስባለሁ፤
10 ፤ ፈርዖን በባሪይዎቹ ላይ ተቆጣ፥ እኔንም የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ በግዞት ስፍራ በዘበኞች አለቃ ቤት አኖረን፤
11 ፤ እኛም በአንዲት ሌሊት ሕልምን አለምን፥ እኔና እርሱ፤ እያንዳንዳችን እንደ ሕልማችን ትርጓሜ አለምን።
12 ፤ በዚያም የዘበኞቹ አለቃ ባሪያ የሆነ አንድ ዕብራዊ ጕልማሳ ከእኛ ጋር ነበረ፤ ለእርሱም ነገርነው፥ ሕልማችንንም ተረጐመልን፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሕልሙ ተረጐመልን።
13 ፤ እንዲህም ሆነ፤ እንደ ተረጐመልን እንደዚያው ሆነ፤ እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስሁ፥ እርሱም ተሰቀለ።
14 ፤ ፈርዖንም ልኮ ዮሴፍን አስጠራ፥ ከግዞት ቤትም አስቸኰሉት፤ እርሱም ተላጨ፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ ፈርዖንም ገባ።
15 ፤ ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። ሕልምን አየሁ፥ የሚተረጕመውም አልተገኘም፤ ሕልምን እንደ ሰማህ፥ እንደ ተረጐምህም ስለ አንተ ሰማሁ።
16 ፤ ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ ብሎ መለሰ። ይህ በእኔ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን ለፈርዖን በደኅንነት ይመልስለታል።
17 ፤ ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ አለው። እነሆ፥ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤
18 ፤ እነሆም፥ ሥጋቸው የወፈረ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ፥ በመስኩም ይሰማሩ ነበር፤
19 ፤ ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደከሙ መልካቸውም እጅግ የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ እንደ እነርሱ መልከ ክፉ ከቶ አላየሁም፤
20 ፤ የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ወፍራሞቹን ሰባት ላሞች ዋጡአቸው፥
21 ፤ በሆዳቸውም ተዋጡ፤ በሆዳቸውም እንደተዋጡ አልታወቀም፥ መልካቸውም በመጀመሪያ እንደ ነበረው የከፋ ነበረ። ነቃሁም።
22 ፤ በሕልሜም እነሆ የዳበሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች በአንድ አገዳ ሲወጡ አየሁ፤
23 ፤ ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደረቁና የሰለቱ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤
24 ፤ የሰለቱት እሸቶች ያማሩትን ሰባቱን እሸቶች ዋጡአቸው። ለሕልም ተርጓሚዎችም ሕልሜን ነገርሁ የሚተረጕምልኝም አጣሁ።
25 ፤ ዮሴፍም ፈርዖንን አለው። የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን ነግሮታል።
26 ፤ ሰባቱ መልካካሞች ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም መልካካሞች እሸቶች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙ አንድ ነው።
27 ፤ ከእነርሱም በኋላ የወጡት የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ የሰለቱትና የምሥራቅ ነፋስ የመታቸው ሰባቱም እሸቶች እነርሱ ራብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ናቸው።
28 ፤ ለፈርዖን የነገርሁት ነገር ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው።
29 ፤ እነሆ በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ፤
30 ፤ ደግሞ ከዚህ በኋላ የሰባት ዓመት ራብ ይመጣል፥ በግብፅ አገር የነበረውም ጥጋብ ሁሉ ይረሳል፤ ራብም ምድርን በጣም ያጠፋል፤
31 ፤ በኋላ ከሚሆነው ከዚያ ራብ የተነሣም በምድር የሆነው ጥጋብ አይታወቅም፥ እጅግ ጽኑ ይሆናልና።
32 ፤ ሕልሙም ለፈርዖን ደጋግሞ መታየቱ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ያደርገዋል።
33 ፤ አሁንም ፈርዖን ብልህና አዋቂ ሰውን ይፈልግ፥ በግብፅ ምድር ላይም ይሹመው።
34 ፤ ፈርዖን በምድር ላይ ሹማምትን ይሹም፤ በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ፍሬ በግብፅ ምድር ሁሉ ከአምስት እጅ አንደኛውን ይውሰድ።
35 ፤ የሚመጡትን የመልካሞቹን ዓመታት እህላቸውን ያከማቹ፤ ስንዴውንም ከፈርዖን እጅ በታች ያኑሩ፥ እህሎችም በከተሞች ይጠበቁ።
36 ፤ በግብፅ ምድር ስለሚሆነው ስለ ሰባቱ ዓመታት ራብ እህሉ ተጠብቆ ይኑር፥ ምድሪቱም በራብ አትጠፋም።
37 ፤ ነገሩም በፈርዖንና በሎሌዎቹ ፊት መልካም ሆነ፤
38 ፤ ፈርዖንም ሎሌዎቹን እንዲህ አላቸው። በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን እንደዚህ ያለ ሰው እናገኛለንን?
39 ፤ ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። እንደ አንተ ያለ ብልህ አዋቂም ሰው የለም፥ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና።
40 ፤ አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፥ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ።
41 ፤ ፈርዖንም ዮሴፍን። በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾምሁህ አለው።
42 ፤ ፈርዖን ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ በዮሴፍ እጅም አደረገው፥ ነጭ የተልባ እግር ልብስንም አለበሰው፥ በአንገቱም የወርቅ ዝርግፍን አደረገለት፤
43 ፤ የእርሱም በምትሆን በሁለተኛይቱ ሰረገላ አስቀመጠው፥ አዋጅ ነጋሪም። ስገዱ እያለ በፊት በፊቱ ይጮኽ ነበር፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ተሾመ።
44 ፤ ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። እኔ ፈርዖን ነኝ፤ በግብፅ አገር ሁሉ ያለ አንተ ማንም እጁንም እግሩንም አያንሣ።
45 ፤ ፈርዖንም የዮሴፍን ስም ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ጠራው፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የDoጥፌራ ልጅ የምትሆን አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በግብፅ ምድር ሁሉ ወጣ።
46 ፤ ዮሴፍም በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊት በቆመ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ የግብፅ ምድርንም ሁሉ ዞረ።
47 ፤ በሰባቱም በጥጋብ ዓመታት የምድሪቱ ፍሬ ክምር ሆነ።
48 ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ ያለውን የሰባቱን ዓመት እህል ሁሉ ሰበሰበ፥ እህልንም በከተሞቹ አደለበ፤ በየከተማይቱ ዙሪያ ያለውን የእርሻውን እህል ሁሉ በዚያው ከተተ።
49 ፤ ዮሴፍም እንደ ባሕር አሸዋ እጅግ ብዙ የሆነ ስንዴን አከማቸ፥ መስፈርን እስኪተው ድረስ፤ ሊሰፈር አልተቻለምና።
50 ፤ ለዮሴፍም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የDoጥፌራ ልጅ አስናት የወለደችለት ሁለት ልጆች የራብ ዘመን ገና ሳይመጣ ተወለዱለት።
51 ፤ ዮሴፍም የበኵር ልጁን ስም ምናሴ ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል። እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት አስረሳኝ፤
52 ፤ የሁለተኛውንም ስም ኤፍሬም ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል። እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ።
53 ፤ በግብፅ ምድር የነበረውም የሰባቱ ዓመት ጥጋብ አለፈ፥
54 ፤ ዮሴፍም እንደ ተናገረ የሰባቱ ዓመት ራብ ጀመረ። በየአገሩም ሁሉ ራብ ሆነ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ ግን እህል ነበረ።
55 ፤ የግብፅ ምድርም ሁሉ ተራበ፥ ሕዝቡም ስለ እህል ወደ ፈርዖን ጮኸ፤ ፈርዖንም የግብፅ ሰዎችን ሁሉ። ወደ ዮሴፍ ሂዱ፥ እርሱ ያላችሁንም ሁሉ አድርጉ አላቸው።
56 ፤ በምድርም ሁሉ ላይ ራብ ሆነ፤ ዮሴፍም እህል ያለበትን ጎተራ ሁሉ ከፍቶ ለግብፅ ሰዎች ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ ራብም በግብፅ ምድር ጸንቶ ነበር።
57 ፤ አገሮችም ሁሉ እህል ይገዙ ዘንድ ወደ ግብፅ ወደ ዮሴፍ መጡ፤ በምድር ሁሉ ራብ እጅግ ጸንቶ ነበርና።