ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 9

እስራኤል ሆይ፥ ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፤ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የግልሙትናን ዋጋ ወድደሃል።
2 ፤ አውድማውና መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ ጉሽ ጠጅም ይጐድልባታል።
3 ፤ በእግዚአብሔር ምድር ላይ አይቀመጡም፤ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኩስን ነገር ይበላሉ።
4 ፤ ለእግዚአብሔርም የወይን ጠጅን ቁርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ የኀዘንም እንጀራ ይሆንላቸዋል፥ የሚበላውም ሁሉ ይረክሳል፤ እንጀራቸውም ለሰውነታቸው ይሆናል እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገባም።
5 ፤ በዓመት በዓል ቀንና በእግዚአብሔር በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ?
6 ፤ እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ሄዱ፥ ግብጽም ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፤ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል።
7 ፤ የበቀል ወራት መጥቶአል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ያውቃል፤ ከኃጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሰንፎአል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል።
8 ፤ ኤፍሬም ከአምላኬ ጋር ተመልካች ነበረ፤ አሁን ግን ነቢዩ በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ ሆነ፥ በአምላኩም ቤት ጠላትነት አለ።
9 ፤ በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይበቀላል።
10 ፤ እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በkWraት ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥
11 ፤ የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም።
12 ፤ ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ሰው እንዳይቀርላቸው ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፤ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!
13 ፤ እኔ እንዳየሁ የኤፍሬም ልጆች ለምርኮ ተሰጥተዋል፤ ኤፍሬምም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል።
14 ፤ አቤቱ፥ ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው።
15 ፤ ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፤ በዚያ ጠልቻቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው።
16 ፤ ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፤ ደግሞም ቢወልዱ የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ።
17 ፤ አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ።