ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 14

እስራኤል ሆይ፥ በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ።
2 ፤ ከእናንተ ጋር ቃልን ውሰዱ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተመልሳችሁ። ኃጢአትን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በወይፈንም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን።
3 ፤ አሦር አያድነንም፤ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፤ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ። አምላኮቻችን ናችሁ አንላቸውም በሉት።
4 ፤ ቍጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ዓመፃቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወድዳቸዋለሁ።
5 ፤ ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሩን ይሰድዳል።
6 ፤ ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል።
7 ፤ ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ ከእህሉም የተነሣ ይጠግባሉ፤ እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ፤ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል።
8 ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ጣዖት ለኤፍሬም ምንድር ነው? እኔ ሰምቼዋለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል።
9 ፤ ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፥ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል።