ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 10

እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያውን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል።
2 ፤ ልባቸው ተከፈለ፤ አሁንም በደላቸውን ይሸከማሉ፤ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል።
3 ፤ አሁንም። ንጉሥ የለንም፥ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፤ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል? ይላሉ።
4 ፤ የማይረባውን ቃል ይናገራሉ፤ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፤ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል።
5 ፤ የሰማርያ ሰዎች ስለ ቤትአዌን እምቦሳ ይፈራሉ፤ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም በኀዘን ይንተባተባሉ።
6 ፤ ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ ወደ አሦር ይማረካል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል።
7 ፤ ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች።
8 ፤ የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ ተራሮችንም። ክደኑን፥ ኮረብቶችንም። ውደቁብን ይሉአቸዋል።
9 ፤ እስራኤል ሆይ፥ ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በጊብዓ ላይ ሰልፍ አይደርስባቸውምን?
10 ፤ በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ ስለ ሁለቱም ኃጢአታቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ ይሰበሰቡባቸዋል።
11 ፤ ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል።
12 ፤ እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ።
13 ፤ ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና።
14 ፤ በሕዝብህም መካከል ሽብር ይነሣል፤ እናትም ከልጆችዋ ጋር በተፈጠፈጠች ጊዜ ሰልማን ቤትአርብኤልን በሰልፍ ቀን እንዳፈረሰ፥ አምባዎችህ ሁሉ ይፈርሳሉ።
15 ፤ ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ ቤቴል እንዲሁ ያደርግባችኋል፤ በነጋ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።