ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 11

እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት።
2 ፤ አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፤ ለበኣሊምም ይሠዉ ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር።
3 ፤ እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ በእግሩ እንዲሄድ መራሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም።
4 ፤ በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው።
5 ፤ ወደ እኔ ይመለሱ ዘንድ አልወደዱምና ወደ ግብጽ ምድር ይመለሳሉ፥ አሦርም ንጉሣቸው ይሆናል።
6 ፤ ከመከሩትም ምክር የተነሣ ሰይፍ በከተሞቻቸው ላይ ይወድቃል፥ ከበርቴዎችንም ያጠፋል።
7 ፤ ሕዝቤም ከእኔ ይመለሱ ዘንድ ወደዱ፤ ወደ ላይም ቢጠሩአቸው ማንም ከፍ ከፍ ያደርጋቸው ዘንድ አይችልም።
8 ፤ ኤፍሬም ሆይ፥ እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ፥ እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴትስ እንደ አዳማ እጥልሃለሁ? እንዴትስ እንደ ሲባዮ አደርግሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፥ ምሕረቴም ተነሣሥታለች።
9 ፤ እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም አጠፋ ዘንድ አልመለስም፤ በመዓትም አልመጣም።
10 ፤ እግዚአብሔርን ይከተላሉ፥ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ ባገሣም ጊዜ ልጆች እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ።
11 ፤ እንደ ወፍም ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ በቤታቸውም አኖራቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
12