ትንቢተ ሆሴዕ
ምዕራፍ 4
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
2 ፤ እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፤ ደምም ወደ ደም ደርሶአል።
3 ፤ ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ።
4 ፤ ነገር ግን ሕዝብህ ከካህን ጋር እንደሚከራከሩ ናቸውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ።
5 ፤ በቀንም ትሰናከላለህ፥ ነቢዩም ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፤ እናትህንም አጠፋታለሁ።
6 ፤ ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ።
7 ፤ እንደ ብዛታቸው መጠን ኃጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ነውር እለውጣለሁ።
8 ፤ የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አድርገዋል።
9 ፤ እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ ሥራቸውንም እመልስባቸዋለሁ።
10 ፤ እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፥ ሲያመነዝሩም አይበዙም።
11 ፤ ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል።
12 ፤ የግልሙትና መንፈስ ሕዝቤን አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና በትራቸውን ይጠይቃሉ፥ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል።
13 ፤ በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይገለሙታሉ፥ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ።
14 ፤ ወንዶችም ደግሞ ከጋለሞቶች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በገለሞቱ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ይገለበጣል።
15 ፤ እስራኤል ሆይ፥ አንተ ብታመነዝር ይሁዳ አይበድል፤ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም። ሕያው እግዚአብሔርን! ብላችሁ አትማሉ።
16 ፤ እስራኤል እንደ እልከኛ ጊደር እንቢ ብሎአል፤ እግዚአብሔርስ በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን?
17 ፤ ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፤ ተወው።
18 ፤ ስካርን ፈጽመዋል፥ ግልሙትናንም አብዝተዋል፤ አለቆችዋም ነውርን እጅግ ወደዱ።
19 ፤ ነፋስ በክንፍዋ አስሮአታል፤ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ።