ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 8

መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፤ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ንስር ይመጣል።
2 ፤ እነርሱም። አምላክ ሆይ፥ እኛ እስራኤል አወቅንህ ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ።
3 ፤ እስራኤል ደግነትን ጥሎአል፤ ጠላትም ያሳድዱታል።
4 ፤ ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም አደረጉ፥ እኔም አላወቅሁም፤ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው፤ ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ።
5 ፤ ሰማርያ ሆይ፥ እምቦሳህን፤ ጥሎአል፤ ቍጣዬ በላያቸው ነድዶአል፤ እስከ መቼ ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም?
6 ፤ ይህ ደግሞ ከእስራኤል ዘንድ ነው፤ ሠራተኛ ሠራው፥ እርሱም አምላክ አይደለም፤ የሰማርያም እምቦሳ ይቈራረጣል።
7 ፤ ነፍስን ዘርተዋል፥ ዐውሎ ነፍስንም ያጭዳሉ፤ አገዳ የለውም፥ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም እንግዶች ይበሉታል።
8 ፤ እስራኤል ተውጦአል፥ በአሕዛብም መካከል ዛሬ እንደ ረከሰ ዕቃ ሆኖአል።
9 ፤ ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም ወዳጆቹን በእጅ መንሻ ገዛ።
10 ፤ ነገር ግን ለአሕዛብ እጅ መንሻ ቢሰጡ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ ይደክማሉ።
11 ፤ ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያ አብዝቶአልና መሠዊያ ለኃጢአት ይሆንለታል።
12 ፤ የሕጌን ብዛት ጽፌለታለሁ፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጥረውታል።
13 ፤ መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፤ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ።
14 ፤ እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችንም ትበላለች።