ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 13

ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ፍርሃት ነበረ፥ በእስራኤልም ዘንድ ታበየ፤ ነገር ግን በኣልን በማምለክ በበደለ ጊዜ ሞተ።
2 ፤ አሁንም ኃጢአትን ይሠሩ ዘንድ ጨመሩ፤ በብራቸውም ለራሳቸው ቀልጦ የተሠራ ምስልን፥ እንደ ጥበባቸውም ጣዖታትን ሠርተዋል፤ ሁሉም የሠራተኛ ሥራ ናቸው። ስለ እነርሱም። የሚሠዉ ሰዎች እምቦሳውን ይሳሙ ይላሉ።
3 ፤ ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋትም እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፍስም ከአውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ።
4 ፤ እኔ ግን ከግብጽ ምድር ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም።
5 ፤ በምድረ በዳ፥ እጅግ በደረቀ ምድር አውቄህ ነበር።
6 ፤ ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ፤ ስለዚህ ረሱኝ።
7 ፤ ስለዚህም እኔ እንደ አንበሳ ሆንሁባቸው፥ እንደ ነብርም በመንገድ አጠገብ አደባባቸዋለሁ፤
8 ፤ ልጅዋ እንደ ተነጠቀባት ድብ እገጥማቸዋለሁ፥ የልባቸውንም ስብ እቀድዳለሁ፤ በዚያም እንደ አንበሳ እበላቸዋለሁ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይነጣጠቃቸዋል።
9 ፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ በረዳትህ ላይ በመነሣትህ ጥፋትህ ነው።
10 ፤ በየከተማህ ሁሉ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ ወዴት አለ? ስለ እነርሱም። ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ ብለህ የተናገርኸው መሳፍንቶችህ ወዴት አሉ?
11 ፤ በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት።
12 ፤ የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል።
13 ፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ በሚወለድበት ጊዜ በማኅፀን አፍ ቀጥ ብሎ አይወጣምና አእምሮ የሌለው ልጅ ነው።
14 ፤ ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች።
15 ፤ በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆን የምሥራቅ ነፋስ ይመጣል፥ የእግዚአብሔር ነፋስ ከምድረ በዳ ይመጣል፤ ምንጩንም ያደርቃል፥ ፈሳሹንም ያጠፋል፥ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ያሉበትን መዝገብ ይበዘብዛል።
16 ፤ ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጕዞቻቸውም ይቀደዳሉ።