መጽሐፈ ምሳሌ
ምዕራፍ 28
ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል።
2 ስለ አገሪቱ ዓመፀኝነት አለቆችዋ ብዙ ሆኑ፤ በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ግን ዘመንዋ ይረዝማል።
3 ድሆችን የሚያስጨንቅ ምስኪን ሰው እህልን እንደሚያጠፋ እንደ ዶፍ ዝናብ ነው።
4 ሕግን የሚተዉ ሰዎች ኀጥኣንን ያመሰግናሉ፤ ሕግ ጠባቂዎች ግን ይጠሉአቸዋል።
5 ክፉዎች ሰዎች ፍርድን አያስተውሉም፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ።
6 በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ባለጠጋ ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል።
7 ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን አባቱን ያሳፍራል።
8 በአራጣ ብዛትና በቅሚያ ሀብቱን የሚያበዛ ለድሀ ለሚራራ ያከማችለታል።
9 ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት።
10 ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚያስት፥ እርሱ ወደ ጕድጓዱ ይወድቃል፤ ፍጹማን ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ።
11 ባለጠጋ ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል፤ አስተዋይ ድሀ ግን ይመረምረዋል።
12 ጻድቃን ድል ባደረጉ ጊዜ ብዙ ክብር አለ፤ ኀጥኣን ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ ግን ሰው ይሸሸጋል።
13 ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።
14 ሁልጊዜ የሚፈራ ሰው ምስጉን ነው፤ ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ላይ ይወድቃል።
15 በድሀ ሕዝብ ላይ የሚገዛ ክፉ መኰንን እንደሚያገሣ አንበሳን እንደ ተራበ ድብ ነው።
16 አእምሮ የጐደለው መኰንን ትልቅ ግፈኛ ነው፤ ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል።
17 የሰው ደም ያለበት ሰው እንደ ጕድጓድ ይሸሻል፥ ማንም አያስጠጋውም።
18 በቅንነት የሚሄድ ይድናል፤ በጠማምነት የሚሄድ ግን ወዲያው ይወድቃል።
19 ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን ድህነት ይሞላበታል።
20 የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም።
21 ማድላት፥ በቍራሽ እንጀራም መበደል መልካም አይደለም።
22 ምቀኛ ሰው ባለጠጋ ለመሆን ይቸኵላል ችጋርም እንደሚመጣበት አያውቅም።
23 ምላሱን ከሚያጣፍጥ ይልቅ ሰውን የሚገሥጽ በኋላ ሞገስ ያገኛል።
24 ከአባቱና ከእናቱ የሚሰርቅ። ኃጢአትን አልሠራሁም የሚልም የአጥፊ ባልንጀራ ነው።
25 የሚጐመጅ ሰው ክርክርን ያነሣሣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይጠግባል።
26 በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል።
27 ለድሀ የሚሰጥ አያጣም፤ ዓይኖቹን የሚጨፍን ግን እጅግ ይረገማል።
28 ኀጥአን በተነሡ ጊዜ ሰዎች ይሸሸጋሉ፤ እነርሱ በጠፉ ጊዜ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።