ምዕራፍ 23

ከመኰንን ጋር ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥ በፊትህ ያለውን በደኅና አስተውል፤
2 ሰውነትህም ቢሳሳ፥ በጕሮሮህ ላይ ካራ አድርግ።
3 ጣፋጩ መብል አይመርህ የሐሰት እንጀራ ነውና።
4 ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው።
5 በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና።
6 የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤
7 በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም።
8 የበላኸውን መብል ትተፋዋለህ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋዋለህ።
9 በሰነፍ ጆሮ አንዳች አትናገር፥ የቃልህን ጥበብ ያፌዝብሃልና።
10 የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፤ ወደ ድሀ አደጎች እርሻ አትግባ፤
11 ታዳጊአቸው ጽኑ ነውና፥ እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና።
12 ልብህን ለተግሣጽ ስጥ፥ ጆሮህንም ወደ እውቀት ቃል።
13 ሕፃንን ከመቅጣት ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታው አይሞትምና።
14 በበትር ትመታዋለህ፥ ነፍሱንም ትታደጋለህ።
15 ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ቢሆን ልቤ ደግሞ ደስ ይለዋል፤
16 ከንፈሮችህም በቅን ቢናገሩ ኵላሊቶቼ ደስ ይላቸዋል።
17 ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፤
18 በእውነት ፍጻሜ አለህና፥ ተስፋህም አይጠፋምና።
19 ልጄ ሆይ፥ ስማ ጠቢብም ሁን ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ።
20 የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ ለሥጋም ከሚሣሡ ጋር፤
21 ሰካርና ሆዳም ይደኸያሉና፥ የእንቅልፍም ብዛት የተቦጫጨቀ ጨርቅ ያስለብሳልና።
22 የወለደህን አባትህን ስማ፥ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።
23 እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም።
24 የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፥ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል።
25 አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፥ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት።
26 ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ፤
27 ጋለሞታ ሴት የጠለቀች ዐዘቅት ናትና፥ ሌላይቱም ሴት የጠበበች ጕድጓድ ናትና።
28 እንደ ሌባ ታደባለች ወስላቶችንም በሰው ልጆች መካከል ታበዛለች።
29 ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው?
30 የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን?
31 ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ።
32 በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል።
33 ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል።
34 በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥ በደቀልም ላይ እንደ ተኛ።
35 መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፤ ጐሰሙኝ፥ አላወቅሁምም። መቼ እነሣለሁ? ደግሞ ጨምሬ እሻታለሁ ትላለህ።