መጽሐፈ ምሳሌ
ምዕራፍ 19
በከንፈሩ ከሚወሳልት ሰነፍ ይልቅ ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል።
2 ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ እግሩንም የሚያፈጥን ከመንገድ ይስታል።
3 የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፤ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቈጣል።
4 ባለጠግነት ብዙ ወዳጆች ይጨምራል፤ የድሀ ወዳጅ ግን ከእርሱ ይርቃል።
5 ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፥ በሐሰትም የሚናገር አያመልጥም።
6 ብዙ ሰዎች ለጋሱን ያቈላምጣሉ፥ ስጦታ ለሚሰጥም ሁሉ ወዳጅ ነው።
7 ድሀን ሰው ወንድሞቹ ሁሉ ይጠሉታል፤ ይልቁንም ወዳጆቹ ከእርሱ ይርቃሉ። እነርሱንም በቃል ቢከተላቸው አንዳች አይረቡትም።
8 ጥበብን የሚያገኝ ነፍሱን ይወድዳል፥ ማስተዋልንም የሚጠብቅ መልካም ነገርን ያገኛል።
9 ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፤ በሐሰትም የሚናገር ይጠፋል።
10 ለሰነፍ ቅምጥልነት አይገባውም፥ ይልቁንም ባሪያ በአለቆች ላይ ይገዛ ዘንድ።
11 ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቍጣ ያዘገየዋል፥ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል።
12 እንደ አንበሳ ግሣት የንጉሥ ቍጣ ነው፥ ሞገሱም በመስክ ላይ እንዳለ ጠል ነው።
13 ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ኀዘን ነው፥ ጠበኛም ሚስት እንደማያቋርጥ ነጠብጣብ ናት።
14 ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት።
15 ተግባር መፍታት እንቅልፍን ታመጣለች፥ የታካችም ነፍስ ትራባለች።
16 ትእዛዝን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ መንገዱን ቸል የሚል ግን ይጠፋል።
17 ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል።
18 ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፥ መሞቱንም አትሻ።
19 ንዴተኛ ሰው መቀጮ ይከፍላል፤ ብታድነውም ደግሞ ትጨምራለህ።
20 ምክርን ስማ፥ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ።
21 በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል።
22 የሰው ቸርነት የእርሱ ፍሬ ነው፤ ከሐሰተኛ ባለጠጋም እውነተኛ ድሀ ይሻላል።
23 እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤ የሚፈራውም ጠግቦ ይኖራል፥ ክፉ ነገርም አያገኘውም።
24 ታካች ሰው እጁን በወጭቱ ያጠልቃታል፥ ወደ አፉ ስንኳ አይመልሳትም።
25 ፌዘኛ ብትገርፈው አላዋቂ ብልሃተኛ ይሆናል፤ አስተዋይን ሰው ብትገሥጸው እውቀትን ያገኛል።
26 አባቱን የሚያስከፋ እናቱንም የሚያሳድድ የሚያሳፍርና ጐስቋላ ልጅ ነው።
27 ልጅ ሆይ፥ ተግሣጽን ከሰማህ በኋላ ከእውቀት ቃል መሳሳትን ተው።
28 ወስላታ ምስክር በፍርድ ያፌዛል፥ የኀጥኣንም አፍ ክፋትን ይውጣል።
29 ለሚያፌዙ ሰዎች ፍርድ ተዘጋጅታለች፥ ለሰነፎችም ጀርባ በትር።