ምዕራፍ 1

የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤
2 ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፥
3 የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፥
4 ብልሃትን ለአላዋቂዎች ይሰጥ ዘንድ ለጐበዛዝትም እውቀትንና ጥንቃቄን፥
5 ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል።
6 ምሳሌንና ትርጓሜን የጠቢባንና ቃልና የተሸሸገውን ነገር ለማስተዋል።
7 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
8 ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናንትህንም ሕግ አትተው፤
9 ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና።
10 ልጄ ሆይ፥ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል።
11 ደምን ለማፍሰስ ለእኛ ጋር ና እናድባ፥ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን እንሸምቅበት ቢሉ፤
12 በሕይወታቸው ሳሉ እንደ ሲኦል ሆነን እንዋጣቸው፥ በሙሉም ወደ ጕድጓድ እንደሚወድቁ ይሁኑ፤
13 መልካሙን ሀብት ሁሉ እናገኛለን፥ ከምርኮውም ቤታችንን እንሞላለን፤
14 ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፤ ለሁላችንም አንድ ከረጢት ይሁን ቢሉ፤
15 ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥ ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ፤
16 እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና።
17 መርበብ በወፎች ዓይን ፊት በከንቱ ትተከላለችና።
18 እነርሱም በደማቸው ላይ ያደባሉ፥ በነፍሳቸውም ላይ ይሸምቃሉ።
19 እንዲሁ ይህ መንገድ ትርፍን ለማግኘት የሚሳሳ ሁሉ ነው። የባለቤቱን ነፍስ ይነጥቃል።
20 ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፤ በአደባባይ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤
21 በአደባባይ ትጣራለች፤ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች።
22 እናንተ አላዋቂዎች፥ እስከ መቼ አላዋቂነት ትወድዳላችሁ? ፌዘኞችም ፌዝን ይፈቅዳሉ? ሰነፎችም እውቀትን ይጠላሉ?
23 ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፤ እነሆ፥ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ፤ ቃሌን አስተምራችኋለሁ።
24 በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፥ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም ስላላስተዋለ፥
25 ምክሬን ሁሉ ግን ቸል ስላላችሁ፥ ዘለፋዬንም ስላልፈቀዳችሁ፤
26 እኔም ስለዚህ በጥፋታችሁ እስቃለሁ፤ ጥፋታችሁም በመጣ ጊዜ አላግጥባችvሁ።
27 ድንጋጤ እንደ ጐርፍ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ጥፋታችሁም እንደ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ፥ ጭንቅና መከራ በወረደባችሁ ጊዜ።
28 የዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፥ እኔ ግን አልመልስም፤ ተግተው ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም።
29 እውቀትን ጠልተዋልና፥ እግዚአብሔርንም መፍራት አልመረጡምና፤
30 ምክሬን አልፈቀዱምና፥ ዘለፋዬንም ሁሉ ንቀዋልና፤
31 ስለዚህ የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፥ ከራሳቸው ምክር ይጠግባሉ።
32 አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና።
33 የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።