መጽሐፈ ምሳሌ
ምዕራፍ 12
ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፤ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው።
2 ደኅና ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል፤ ተንኰለኛውን ሰው ግን ይቀሥፈዋል።
3 ሰውን ዓመፃ አያጸናውም፤ የጻድቃን ሥር ግን አይንቀሳቀስም።
4 ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት።
5 የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፤ የኃጥኣን ምክር ግን ተንኰል ነው።
6 የኃጥኣን ቃል ደምን ለማፍሰስ ትሸምቃለች፤ የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል።
7 ኀጥኣን ይገለበጣሉ፥ ደግሞም አይገኙም፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።
8 ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ ልቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል።
9 ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል።
10 ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው።
11 ምድሩን የሚሠራ ሰው እንጀራ ይጠግባል፤ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን አእምሮ የጐደለው ነው።
12 የኅጥኣን ፈቃድ የክፉዎች ወጥመድ ናት፤ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል።
13 ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፤ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል።
14 የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል።
15 የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል።
16 የሰነፍ ቍጣ ቶሎ ይታወቃል፤ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል።
17 እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፤ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል።
18 እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።
19 የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች፤ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው።
20 ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፤ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው።
21 ጻድቅን መከራ አያገኘውም፤ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው።
22 ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አሰጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።
23 ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፤ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል።
24 የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች።
25 ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።
26 ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፤ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች።
27 ታካች ሰው አደን ምንም አያድንም፤ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው።
28 በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ በጎዳናዋም ሞት የለም።