ምዕራፍ 14

ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፤ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች።
2 በቅን የሚሄድ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል።
3 በሰነፍ አፍ የትዕቢት በትር አለ፤ የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች።
4 በሬ በሌለበት ስፍራ እህል አይገኝም፤ ብዙ ሲሳይ ግን በበሬዎች ኃይል ነው።
5 የታመነ ምስክር አይዋሽም፤ የሐሰት ምስክር ግን በሐሰት ይናገራል።
6 ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል አያገኛትም፤ ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም።
7 ከሰነፍ ሰው ፊት ራቅ፥ በእርሱ ዘንድ የእውቀትን ከንፈር አታገኝምና።
8 የብልህ ሰው ጥበብ መንገዱን ያስተውል ዘንድ ነው፤ የሰነፎች ስንፍና ግን ሽንገላ ነው።
9 ሰነፉ በኃጢአት ያፌዛል፤ በቅኖች መካከል ግን ቸርነት አለች።
10 የራሱን ኀዘን ልብ ያውቃል፤ ከደስታውም ጋር ሌላ ሰው አይገናኝም።
11 የኅጥኣን ቤት ይፈርሳል፤ የቅኖች ማደሪያ ግን ያብባል።
12 ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።
13 በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው።
14 ልቡን ከጽድቅ የሚመልስ ሰው ከመንገዱ ፍሬ ይጠግባል፥ ጻድቅም ሰው ደግሞ በራሱ።
15 የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።
16 ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፤ ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል።
17 ቍጡ ሰው በስንፍና ይሠራል፤ አስተዋይ ግን ይታገሣል።
18 አላዋቂዎች ሰዎች ስንፍናን ይወርሳሉ፤ ብልሆች ግን እውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ።
19 ኃጢአተኞች በደጎች ፊት ይጐነበሳሉ፥ ኀጥኣንም በጻድቃን በር።
20 ድሀ በባልንጀራው ዘንድ የተጠላ ነው የባለጠጋ ወዳጆች ግን ብዙዎች ናቸው።
21 ባልንጀራውን የሚንቅ ይበድላል ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉ ነው።
22 ክፉ የሚያደርጉ ይስታሉ፤ ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ ናቸው።
23 በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል፤ ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ።
24 የጠቢባን ዘውድ ባለጠግነታቸው ነው፤ የሰነፎች ስንፍና ግን ስንፍና ነው።
25 እውነተኛ ምስክር ነፍሶችን ያድናል፤ በሐሰት የሚናገር ግን ሸንጋይ ነው።
26 እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው፥ ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል።
27 ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘድን እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው።
28 የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፤ በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ።
29 ለትግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቍጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል።
30 ትሑት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፤ ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል።
31 ድሀን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል፤ ለድሀ ምሕረትን የሚያደርግ ግን ያከብረዋል።
32 ኀጥእ በክፋቱ ይደፋል፤ ጻድቅ ግን በእውነቱ ይታመናል።
33 በአዋቂ ልብ ጥበብ ትቀመጣለች፤ በሰነፎች ውስጥ ግን አትታወቅም።
34 ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች።
35 አስተዋይ አገልጋይ በንጉሥ ዘንድ ይወደዳል፤ በሚያሳፍር ላይ ግን ቍጣው ይሆናል።