ምዕራፍ 8

ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አዋረዳቸውም፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ሜቴግ አማ የተባለችውን ከተማ ወሰደ።
2 ፤ ሞዓብን መታ፥ ሞዓባውያንንም በምድር ጥሎ በገመድ ሰፈራቸው፤ በሁለትም ገመድ ለሞት፥ በአንድም ገመድ ሙሉ ለሕይወት ሰፈራቸው፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት።
3 ፤ ዳዊትም ደግሞ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ የረአብን ልጅ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን መታ።
4 ፤ ዳዊትም ከእርሱ ሺህ ሰባት መቶ ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ያዘ፤ ዳዊትም የሰረገለኛውን ፈረስ ሁሉ ቋንጃ ቈረጠ፤ ለመቶ ሰረገላ ብቻ አስቀረ።
5 ፤ ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደለ።
6 ፤ ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፥ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው።
7 ፤ ዳዊትም ለአድርአዛር ባሪያዎች የነበሩትን የወርቅ ጋሾች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ።
8 ፤ ንጉሡም ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከቤጣሕና ከቤሮታይ እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ።
9 ፤ የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ።
10 ፤ ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ድል ስለ መታ ቶዑ ልጁን አዶራምን ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ፥ ይመርቀውም ዘንድ ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የብርና የወርቅ የናስም ዕቃ ይዞ መጣ።
11
12 ፤ ንጉሥ ዳዊትም ካሸነፋቸው ከአሕዛብ ሁሉ ከሶርያ ከሞዓብም ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከረአብም ልጅ ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር ምርኮ ከቀደሰው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ።
13 ፤ ዳዊትም በተመለሰ ጊዜ ከኤዶምያስ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች በጨው ሸለቆ ውስጥ በመምታቱ ስሙ ተጠራ።
14 ፤ በኤዶምያስ ሁሉ ጭፍሮች አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሚሄድበት ሁሉ ድልን ሰጠው።
15 ፤ ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ዳዊትም ለሕዝቡ ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው።
16 ፤ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ፤
17 ፤ የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቢሜሌክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሠራያም ጸሐፊ ነበረ፤
18 ፤ የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች አማካሪዎች ነበሩ።