ምዕራፍ 7

እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ባሳረፈው ጊዜ፥
2 ፤ ንጉሡ ነቢዩን ናታንን። እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ ተቀመጠ እይ አለው።
3 ፤ ናታንም ንጉሡን። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ አለው።
4 ፤ በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው።
5
6 ፤ ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም።
7 ፤ ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ። ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን?
8 ፤ አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፤
9 ፤ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ።
10
11 ፤ ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፤ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋኋላ አይናወጥ፤ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፤ ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ። ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል።
12 ፤ ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ።
13 ፤ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።
14 ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ፤
15 ፤ ከፊቴም ከጣልሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም።
16 ፤ ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል።
17 ፤ እንደዚህ ቃል ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው።
18 ፤ ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ?
19 ፤ ቤቴስ ምንድር ነው? ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ ስለ ባሪያህም ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው።
20 ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድር ነው?
21 ፤ ለባሪያህም ታስታውቀው ዘንድ ስለ ቃልህ ምክንያትና እንደ ልብህ አሳብ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ አደረግህ።
22 ፤ ስለዚህም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ የለምና፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለምና አንተ ታላቅ ነህ።
23 ፤ ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ በአሕዛብና በአምላኮቻቸውም ፊት ከግብጽ በተቤዠው ሕዝብ ፊት ተአምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ሄደለት እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ?
24 ፤ ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነሃቸዋል።
25 ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የተናገርኸውን ለዘላለም አጽናው፥ እንደ ተናገርህም አድርግ።
26 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሁን፤ የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።
27 ፤ አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ። እኔ ቤት እሠራልሃለሁ ብለህ ለባሪያህ ገልጠሃልና ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ ደፈረ።
28 ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አሁንም አንተ አምላክ ነህ፥ ቃልህም እውነት ነው፥ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል።
29 ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተናግረሃልና አሁን እንግዲህ ለዘላለም በፊትህ ይሆን ዘንድ የባሪያህን ቤት፥ እባክህ፥ ባርክ፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረክ።