ምዕራፍ 10

ከዚህ በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ሞተ፥ ልጁም ሐኖን በፋንታው ነገሠ።
2 ፤ ዳዊትም። አባቱ ወረታ እንዳደረገልኝ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው ባሪያዎቹን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ወደ አሞን ልጆች አገር መጡ።
3 ፤ የአሞንም ልጆች አለቆች ጌታቸውን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ ሊያጽናናህ ባሪያዎቹን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ዳዊትስ ከተማይቱን ለመመርመርና ለመሰለል ለማጥፋትም ባሪያዎቹን የላከ አይደለምን? አሉት።
4 ፤ ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ የጢማቸውን ገሚስ ላጨ፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው።
5 ፤ ዳዊትም ያን በሰማ ጊዜ ሰዎቹ እጅግ አፍረው ነበሩና ተቀባዮች ላከ። ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አላቸው።
6 ፤ የአሞን ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደተጠሉ ባዩ ጊዜ፥ የአሞን ልጆች ልከው ከሶርያውያን ከቤትሮዖብና ከሱባ ሀያ ሺህ እግረኞች፥ ከመዓካ ንጉሥም አንድ ሺህ ሰዎች፥ ከጦብም አሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ።
7 ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ።
8 ፤ የአሞንም ልጆች ወጥተው በበሩ መግቢያ ፊት ለፊት ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን፥ የጦብና የመዓካም ሰዎች ለብቻቸው በሰፊ ሜዳ ላይ ነበሩ።
9 ፤ ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦቹን ሁሉ መረጠ፥ በሶርያውያንም ፊት ለሰልፍ አኖራቸው።
10 ፤ የቀረውንም ሕዝብ በወንድሙ በአቢሳ እጅ አድርጎ በአሞን ልጆች ፊት ለሰልፍ አኖራቸው።
11 ፤ ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ትረዳኛለህ፤ የአሞን ልጆች ቢበረቱብህ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ።
12 ፤ አይዞህ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።
13 ፤ ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ከሶርያውያን ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ።
14 ፤ የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ፤ ኢዮአብም ከአሞን ልጆች ዘንድ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
15 ፤ ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ በአንድነት ተሰበሰቡ።
16 ፤ አድርአዛርም ልኮ በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን፥ አመጣ፤ ወደ ኤላምም መጡ፥ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሶባክ በፊታቸው ነበረ።
17 ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ ወደኤላም መጣ፤ ሶርያውያንም በዳዊት ፊት ተሰልፈው ከእርሱ ጋር ተዋጉ።
18 ፤ ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት መቶ ሰረገለኞች አርባ ሺህም ፈረሰኞች ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሶባክን መታ፥ እርሱም በዚያ ሞተ።
19 ፤ ለአድርአዛርም የሚገብሩ ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ታረቁ፥ ገበሩላቸውም። ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ ፈሩ።