ምዕራፍ 2

ከዚያም በኋላ ዳዊት። ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። ውጣ አለው። ዳዊትም። ወዴት ልውጣ? አለ። እርሱም። ወደ ኬብሮን ውጣ አለው።
2 ፤ ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ።
3 ፤ ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎችና ቤተ ሰባቸውን ሁሉ አመጣ፤ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ።
4 ፤ የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳዊት ነገሩት።
5 ፤ ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው። እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ።
6 ፤ አሁንም እግዚአብሔር ቸርነትንና እውነትን ያድርግላችሁ፤ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን ቸርነት እመልስላችኋለሁ።
7 ፤ አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፥ እናንተም ጨክኑ፤ ዳግም የይሁዳ ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል።
8 ፤ የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደመሃናይም አሻገረው፤
9 ፤ በገለዓድና በአሹራውያን በኢይዝራኤልም በኤፍሬምም በብንያምም በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው።
10 ፤ የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ፤ ነገር ግን የይሁዳ ቤት ዳዊትን ተከተለ።
11 ፤ ዳዊትም በይሁዳ ቤት ነግሦ በኬብሮን የተቀመጠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።
12 ፤ የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ባሪያዎች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ።
13 ፤ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ባሪያዎች ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፤ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ።
14 ፤ አበኔርም ኢዮአብን። ጕልማሶች ይነሡ፥ በፊታችንም ይቈራቈሱ አለው፤ ኢዮአብም። ይነሡ አለ።
15 ፤ ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ አስራ ሁለት፥ ከዳዊትም ባሪያዎች አሥራ ሁለት ተቈጥረው ተነሡ።
16 ፤ ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በወደረኛው ጎን ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም የስለታም ሰይፍ እርሻ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በገባዖን ነው።
17 ፤ በዚያም ቀን ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳዊትም ባሪያዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ።
18 ፤ በዚያም ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ አሣሄልም ነበሩ፤ አሣሄልም እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ።
19 ፤ አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፥ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም።
20 ፤ አበኔርም ዘወር ብሎ ተመለከተና። አንተ አሣሄል ነህን? አለ። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
21 ፤ አበኔርም። ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ አንድ ጕልማሳ ያዝ፥ መሣርያውንም ውሰድ አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ።
22 ፤ አበኔርም አሣሄልን። ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅኝቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? አለው።
23 ፤ ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ፤ አበኔርም በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በኋላው ወጣ፥ በዚያም ስፍራ ወድቆ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበቱ ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር።
24 ፤ ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፤ በገባዖንም ምድረ በዳ መንገድ በጋይ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማ ኮረብታ ድረስ በወጡ ጊዜ ፀሐይ ጠለቀች።
25 ፤ የብንያምም ልጆች ወደ አበኔር ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፥ በኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ።
26 ፤ አበኔርም ወደ ኢዮአብ ጮኸ። ሰይፍ በውኑ እስከ ዘላለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው? አለው።
27 ፤ ኢዮአብም። ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ በጥዋት ወጥተው በሄዱ ነበር፥ ወንድሞቻቸውንም ማሳደድ በተዉ ነበር አለ።
28 ፤ ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም ሁሉ ቆመ፥ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደደም፥ ሰልፍም አላደረገም።
29 ፤ አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ዓረባ እያለፉ ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ ቢትሮንንም ሁሉ ካለፉ በኋላ ወደ መሃናይም መጡ።
30 ፤ ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከአሣሄል ሌላ አሥራ ዘጠኝ ሰዎች ጐደሉ።
31 ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ከብንያምና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ያህል ገደሉ።
32 ፤ አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፤ ኢዮአብና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ።