ምዕራፍ 18

ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ሻለቆችንና የመቶ አለቆችንም ሾመላቸው።
2 ፤ ዳዊትም ሕዝቡን ከኢዮአብ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከኢዮአብም ወንድም ከጽሩያ ልጅ ከአቢሳ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከጌት ሰውም ከኢታይ እጅ በታች ሲሶውን ሰደደ። ንጉሡም ሕዝቡን። እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር እወጣለሁ አላቸው።
3 ፤ ሕዝቡ ግን። አትወጣም፤ ብንሸሽ ስለ እኛ አያስቡም፤ ከእኛም እኩሌታው ቢሞት ስለ እኛ አያስቡም፤ አንተ ግን ለብቻህ ከእኛ ከአስሩ ሺህ ይልቅ ትበልጣለህ፤ አሁንም በከተማ ተቀምጠህ ብትረዳን ይሻላል አሉ።
4 ፤ ንጉሡም። መልካም የሚመስላችሁን አደርጋለሁ አላቸው። ንጉሡም በበሩ አጠገብ ቆመ፥ ሕዝቡም ሁሉ መቶ በመቶ ሺህ በሺህ እየሆኑ ወጡ።
5 ፤ ንጉሡም እዮአብንና አቢሳን ኢታይንም። ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡም ስለአቤሴሎም አለቆቹን ሁሉ ሲያዝዝ ሕዝቡ ሁሉ ሰማ።
6 ፤ ሕዝቡም በእስራኤል ላይ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ሰልፉም በኤፍሬም ሁሉ ውስጥ ሆነ።
7 ፤ በዚያም የእስራኤል ሕዝብ በዳዊት ባሪያዎች ፊት ተመቱ፥ በዚያም ቀን ታላቅ ውጊያ በዚያ ሆነ፥ ሃያ ሺህ ሰውም ሞተ።
8 ፤ ከዚያም ሰልፉ በአገሩ ሁሉ ፊት ላይ ተበተነ፤ በዚያም ቀን ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ።
9 ፤ አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር፥ በቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ፥ ራሱም በዛፉ ተያዘ፤ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፥ ተቀምጦበትም የነበረ በቅሎ አለፈ።
10 ፤ አንድ ሰውም አይቶ። እነሆ፥ አቤሴሎም በትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁ ብሎ ለኢዮአብ ነገረው።
11 ፤ ኢዮአብም ለነገረው ሰው። እነሆ፥ ካየኸው ለምን ወደ ምድር አልመታኸውም? አስር ብርና አንድ ድግ እሰጥህ ነበር አለው።
12 ፤ ሰውዮውም ኢዮአብን። እኛ ስንሰማ ንጉሡ አንተንና አቢሳን ኢታይንም። ብላቴናውን አቤሴሎምን ማንም እንዳይነካው ተጠንቀቁ ብሎ አዝዞአልና ሺህ ብር በእጄ ላይ ብትመዝን እጄን በንጉሡ ልጅ ላይ ባልዘረጋሁም ነበር።
13 ፤ እኔ ቅሉ በነብሱ ላይ ብወነጅል ኖሮ ይህ ከንጉሥ ባልተሰወረም፥ አንተም በተነሳህብኝ ነበር አለው።
14 ፤ ኢዮአብም። እኔ ከአንተ ጋር እንዲህ እዘገይ ዘንድ አልችልም ብሎ ሦስት ጦሮች በእጁ ወሰደ፥ አቤሴሎምም ገና በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሕያው ሳለ በልቡ ላይ ተከላቸው።
15 ፤ አስሩም የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ከበቡት፥ አቤሴሎምንም መትተው ገደሉት።
16 ፤ ኢዮአብም ሕዝቡን ከልክሎ ነበርና ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ።
17 ፤ አቤሴሎምንም ወስደው በዱር ባለ በታላቅ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፥ እጅግም ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
18 ፤ አቤሴሎምም ሕያው ሳለ። ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሃውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፤ ሃውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ የአቤሴሎም መታሰቢያ ተብሎ ይጠራል።
19 ፤ የሳዶቅ ልጅ አኪማኣስ ግን። እግዚአብሔር ጠላቶቹን እንደተበቀለለት ሮጬ ለንጉሥ የምሥራች ልንገር አለ።
20 ፤ ኢዮአብም። በሌላ ቀን እንጂ ዛሬ ወሬ አትናገርም፤ የንጉሥ ልጅ ሞቶአልና ዛሬ ወሬ አትናገርም አለው።
21 ፤ ኢዮአብም ኵሲን። ሂድ ያየኸውንም ለንጉሡ ንገር አለው። ኵሲም ለኢዮአብ እጅ ነስቶ ሮጠ።
22 ፤ ዳግመኛም የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ኢዮአብን። የሆነ ሆኖ ኵሲን ተከትዬ፥ እባክህ፥ ልሩጥ አለው። ኢዮአብም። ልጄ ሆይ፥ መልካም ወሬ የምትወስድ አይደለህምና ትሮጥ ዘንድ ለምን ትወድዳለህ? አለ።
23 ፤ እርሱም። እኔ ብሮጥ ምን ይገድዳል? አለ። እርሱም። ሩጥ አለው። አኪማአስም በሜዳው መንደር በኩል ሮጠ፥ ኵሲንም ቀደመው።
24 ፤ ዳዊትም በሁለት በር መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ዘበኛውም በቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ወጣ፥ ዓይኑንም አቅንቶ ብቻውን የሚሮጥ ሰው አየ።
25 ፤ ዘበኛውም ለንጉሡ ሊነግረው ጮኸ። ንጉሡም። ብቻውን እንደሆነ በአፉ ወሬ ይኖራል አለ።
26 ፤ እርሱም ፈጥኖ ቀረበ። ዘበኛውም ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፤ ዘበኛውም ለደጅ ጠባቂው ጮኾ። እነሆ፥ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አየሁ አለ። ንጉሡም። እርሱ ደግሞ ወሬ ይዞ ይሆናል አለ።
27 ፤ ዘበኛውም። የፊተኛው ሩጫ እንደ ሳዶቅ ልጅ እንደ አኪማአስ ሩጫ ይመስላል አለ፤ ንጉሡም። እርሱ መልካም ሰው ነው፥ መልካምም ወሬ ያመጣል አለ።
28 ፤ አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን። ሁሉ ደህና ሆኖአል አለው። በንጉሡም ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ተደፍቶ። በንጉሡ በጌታዬ ላይ እጃቸውን ያነሱትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።
29 ፤ ንጉሡም። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለ። አኪማአስም። ኢዮአብ እኔን ባሪያህንና የንጉሡን ባሪያ በላከ ጊዜ ትልቅ ሽብር አይቻለሁ፥ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም ብሎ መለሰለት።
30 ፤ ንጉሡም። ፈቀቅ ብለህ ቁም አለ፤ እርሱም ፈቀቅ ብሎ ቆመ።
31 ፤ እነሆም፥ ኵሲ መጣ፤ ኵሲም። እግዚአብሔር በላይህ የተነሡትን ሁሉ ዛሬ እንደተበቀለልህ ለጌታዬ ለንጉሡ ወሬ አምጥቻለሁ አለ።
32 ፤ ንጉሡም ኵሲን። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለው። ኵሲም። የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች፥ በክፉም የተነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ብላቴና ይሁኑ ብሎ መለሰለት።
33 ፤ ንጉሡም እጅግ አዘነ፥ በበሩም ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም። ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ ይል ነበር። ች