መጽሐፈ ሳሙኤል ካል
ምዕራፍ 23
የዳዊትም የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብም አምላክ የተቀባው፥ በእስራኤል ዘንድ መልካም ባለ ቅኔ የሆነ፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር፤
2 ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ።
3 ፤ የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ፤ የእስራኤል ጠባቂ እንዲህ አለ። በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን፥ በእግዚአብሔርም ፍርሃት የሚነግሥ፥
4 ፤ እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን እንደ ፀሐይ አወጣጥ፥ በጥዋትም ያለ ደመና እንደሚደምቅ፥ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል።
5 ፤ በውኑ ቤቴ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁ አይደለምን? ከእኔም ጋር በሁሉ ነገር ቅንና ጽኑ የሆነውን የዘላለም ቃል ኪዳን አድርጎአል፤ መድኃኒቴንና ፈቃዴን ሁሉ ያበቅላል።
6 ፤ ዓመፀኞች ሁሉ ግን ሰው በእጁ እንደማይዘው፥ እንደ ተጣለ እሾህ ናቸው።
7 ፤ ማናቸውም ሰው ይነካው ዘንድ ቢወደድ፥ በእጁ ብረትና የጦሩን የቦ ይይዛል፤ በሥራቸውም በእሳት ፈጽሞ ይቃጠላሉ።
8 ፤ የዳዊት ኃያላን ስም ይህ ነው። የአለቆች አለቃ የሆነ ከነዓናዊው ኢያቡስቴ ነበረ፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ያህል በአንድ ጊዜ ገደለ።
9 ፤ ከእርሱም በኋላ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልያናን ነበረ፤ ለሰልፍ የተሰበሰቡትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ከሦስቱ ኃያላን አንዱ እርሱ ነበረ፤ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ።
10 ፤ እርሱ ግን ተነሥቶ እጁ እስኪደክምና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ።
11 ፤ ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበረ። ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት እርሻ በአንድነት ሆነው ተከማችተው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ።
12 ፤ እርሱ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ጠበቀ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደለ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ መድኃኒትአደረገ።
13 ፤ ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር።
14 ፤ በዚያ ጊዜም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ።
15 ፤ ዳዊትም። በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ? ብሎ ተመኘ።
16 ፤ ሦስቱም ኃያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፥ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ።
17 ፤ አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ በነፍሳቸው ደፍረው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን? ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው።
18 ፤ የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሠላሳው አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን በሦስቱ መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ተጠርቶ ነበር።
19 ፤ እርሱ በሠላሳው መካከል የከበረ አልነበረምን? ስለዚህ አለቃቸው ሆኖ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም።
20 ፤ በቀብጽኤል የነበረው ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊውን የቀብስኤልን ሁለት ልጆች ገደለ፤ በአመዳዩም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ።
21 ፤ ረጅሙንም ግብጻዊ ሰው ገደለ፤ ግብጻዊው በእጁ ጦር ነበረው፤ በናያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው።
22 ፤ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር።
23 ፤ ከሠላሳውም ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በክብር ዘበኞቹ ላይ ሾመው።
24 ፤ የኢዮአብም ወንድም አሣሄል በሠላሳው መካከል ነበረ፥ የቤተ ልሔም ሰው የዱዲ
25 ፤ ልጅ ኤልያናን፥ አሮዳዊው ሣማ፥ ሒሮዳዊው ኤሊቃ፥
26 ፤ ፈልጣዊው ሴሌስ፥ የቴቁሐዊው
27 ፤ የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው
28 ፤ አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ምቡናይ፥ አሆሃዊው
29 ፤ ጸልሞን፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ወገን
30 ፤ ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው
31 ፤ ሂዳይ፥ ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ በርሑማዊው
32 ፤ ዓዝሞት፥ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥
33 ፤ የአሳን ልጆች፥ ዮናታን፥ አሮዳዊው ሣማ
34 ፤ የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የማዕካታዊው ልጅ የአሐስባይ ልጅ ኤሌፋላት፥ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤልያብ፥
35 ፤ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ አርባዊው ፈዓራይ፥
36 ፤ የሱባ ሰው የናታን ልጅ ይግዓል፥ ጋዳዊው
37 ፤ ባኒ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች አሞናዊው ጼሌቅ፥ ብኤሮታዊው
38 ፤ ነሃራይ፥ ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው
39 ፤ ጋሬብ፥ ኬጢያዊው ኦርዮ፤ ሁሉ በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው።