ምዕራፍ 4

የሳኦልም ልጅ ኢያቡስቴ አበኔር በኬብሮን እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ እጁ ደከመች፥ እስራኤላውያንም ሁሉ ደነገጡ።
2 ፤ ለሳኦልም ልጅ ለኢያቡስቴ የጭፍራ አለቆች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ የአንዱም ስም በዓና፥ የሁለተኛውም ስም ሬካብ ነበረ፥ ከብንያምም ልጆች የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ነበሩ፤ ብኤሮትም ለብንያም ተቈጥራ ነበር።
3 ፤ ብኤሮታውያንም ወደ ጌቴም ሸሽተው ነበር፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ተጠግተው ነበር።
4 ፤ ለሳኦልም ልጅ ለዮናታን አንድ ሽባ የሆነ ልጅ ነበረው። የሳኦልና የዮናታን ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ፥ ሞግዚቱም አዝላው ሸሸች፤ ፈጥናም ስትሸሽ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜምፊቦስቴ ነበር።
5 ፤ የብኤሮታዊውም የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ቀኑ ሲሞቅ ወደ ኢያቡስቴ ቤት መጡ፤ እርሱም በቀትር ጊዜ በምንጣፍ ላይ ተኝቶ ነበር።
6 ፤ በረኛይቱም ስንዴ ታበጥር ነበር፥ አንቀላፍታም ተኝታ ነበር፤ ሬካብና ወንድሙ በዓናም በቀስታ ገቡ።
7 ፤ ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ እርሱ በእልፍኙ በምንጣፉ ላይ ተኝቶ ሳለ መቱት፥ ገደሉትም፤ ራሱንም ቈርጠው ወሰዱት፥ በዓረባም መንገድ ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ።
8 ፤ የኢያቡስቴንም ራስ ይዘው ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጡ፥ ንጉሡንም። ነፍስህን ይሻ የነበረው የጠላትህ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ እነሆ፤ እግዚአብሔርም ዛሬ ከሳኦልና ከዘሩ ለጌታችን ለንጉሥ ተበቀለለት አሉት።
9 ፤ ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞት ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነ ሕያው እግዚአብሔርን!
10 ፤ መልካም ወሬ የያዘ መስሎት። እነሆ፥ ሳኦል ሞተ ብሎ የነገረኝን የምስራቹ ዋጋ እንዲሆን ይዤ በጺቅላግ ገደልሁት።
11 ፤ ይልቁንስ በቤቱ ውስጥ በምንጣፉ ላይ ንጹሑን ሰው የገደላችሁትን እናንተን ኃጢአተኞችንማ እንዴት ነዋ? ደሙን ከእጃችሁ አልሻውምን? ከምድርም አላጠፋችሁምን?
12 ፤ ዳዊትም ጕልማሶቹን አዘዘ፥ ገደሉአቸውም፤ እጃቸውንና እግራቸውን ቈርጠው በኬብሮን በውኃ መቆሚያ አጠገብ አንጠለጠሉአቸው። የኢያቡስቴንም ራስ ወስደው በአበኔር መቃብር በኬብሮን ቀበሩት።