ትንቢተ አሞጽ

1 2 3 4 5 6 7 8 9


ምዕራፍ 9

ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ። መድረኮቹ ይናወጡ ዘንድ ጕልላቶቹን ምታ፥ በራሳቸውም ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም።
2 ፤ ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤
3 ፤ በቀርሜሎስም ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤
4 ፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።
5 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ይዳስሳል እርስዋም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሙላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ደግሞ እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች።
6 ፤ አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው።
7 ፤ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?
8 ፤ እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዓይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋታለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥ ይላል እግዚአብሔር።
9 ፤ እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንዲነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እነፋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።
10 ፤ ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ።
11 ፤ በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤
12 ፤ ይኸውም የኤዶምያስን ቅሬታ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይወርሱ ዘንድ ነው፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።
13 ፤ እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚያገኝበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ተራሮችም በተሀውን የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ።
14 ፤ የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ አታክልትንም ያባጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ።
15 ፤ በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥ ይላል አምላክህ እግዚአብሔር