ትንቢተ አሞጽ

1 2 3 4 5 6 7 8 9


ምዕራፍ 1

በቴቁሔ ከላም ጠባቂዎች መካከል የነበረ አሞጽ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከሆነበቱ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ቃል ይህ ነው።
2 ፤ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ የእረኞችም ማሰማርያዎች ያለቅሳሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።
3 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ገለዓድን በብረት መንኰራኵር አሂዶአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
4 ፤ በአዛሄል ቤት እሳትን እሰድዳለሁ፥ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች።
5 ፤ የደማስቆንም መወርወሪያ እሰብራለሁ፥ ተቀማጮችንም ከአዌን ሸለቆ አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ወደ ቂር ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር።
6 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለኤዶምያስ አሳልፈው ይሰጡአቸው ዘንድ ምርኮኞችን ሁሉ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
7 ፤ በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች።
8 ፤ ተቀማጮችን ከአዛጦን አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምርኮኞችን ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
10 ፤ በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች።
11 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄንም ሁሉ ጥሎአልና፥ ቍጣውም ሁልጊዜ ቀድዶአልና፥ መዓቱንም ለዘላለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
12 ፤ በቴማን ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የባሶራንም አዳራሾች ትበላለች።
13 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዳርቻቸውን ያሰፉ ዘንድ የገለዓድን እርጕዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአሞን ልጆች ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
14 ፤ በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ በሰልፍም ቀን በጩኸት በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት አዳራሾችዋን ትበላለች፤
15 ፤ ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር።