ትንቢተ አሞጽ

1 2 3 4 5 6 7 8 9


ምዕራፍ 5

የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእናንተ ላይ ለሙሾ የማነሣውን ይህን ቃል ስሙ።
2 ፤ የእስራኤል ድንግል ወደቀች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሣም፤ በምድርዋ ላይ ተጣለች፥ የሚያስነሣትም የለም።
3 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላልና። ሺህ ከሚወጣባት ከተማ መቶ ይቀርላታል፥ መቶም ከሚወጣባት ከተማ ለእስራኤል ቤት አሥር ይቀርላታል።
4 ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና። እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤
5 ፤ ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም ከንቱ ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፥ ወደ ጌልገላም አትግቡ፥ ወደ ቤርሳቤህም አትለፉ።
6 ፤ በዮሴፍ ቤት እሳት እንዳትቃጠል፥ በቤቴል የሚያጠፋትም ሳይኖር እንዳትበላ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
7 ፤ ፍርድን ወደ እሬት የምትለውጡ፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የምትጥሉ እናንተ ሆይ፥
8 ፤ ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮን የተባለውን ኮከብ የፈጠረውን፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጠውን፥ ቀኑንም በሌሊት የሚያጨልመውን፥ የባሕሩንም ውኆች ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሳቸውን፥
9 ፤ አምባውም እንዲፈርስ በብርቱ ላይ የድንገት ጥፋት የሚያመጣውን ፈልጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው።
10 ፤ በበሩ አደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ።
11 ፤ ድሀውንም ደብድባችኋልና፥ የስንዴውንም ቀረጥ ከእርሱ ወስዳችኋልና ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ሠርታችኋል፥ ነገር ግን አትቀመጡባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎች ተክላችኋል፥ ነገር ግን ከወይን ጠጃቸው አትጠጡም።
12 ፤ ጻድቁን የምታስጨንቁ፥ ጉቦንም የምትቀበሉ፥ በበሩም አደባባይ የችጋረኛውን ፍርድ የምታጣምሙ እናንተ ሆይ፥ በደላችሁ እንዴት እንደ በዛ፥ ኃጢአታችሁም እንዴት እንደ ጸና እኔ አውቃለሁና።
13 ፤ ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና በዚያ ዘመን አስተዋይ የሚሆን ዝም ይላል።
14 ፤ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ እንዲህም እናንተ እንደ ተናገራችሁ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል።
15 ፤ ክፉውን ጥሉ፥ መልካሙንም ውደዱ፥ በበሩም አደባባይ ፍርድን አጽኑ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ቅሬታ ይራራ ይሆናል።
16 ፤ ስለዚህ ጌታ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በየአደባባዩ ሁሉ ላይ ዋይታ ይሆናል፤ በየመንገዱም ሁሉ ላይ ወዮ ወዮ ይባላል፤ ገበሬዎቹም ወደ ልቅሶ፥ አልቃሾቹም ወደ ዋይታ ይጠራሉ።
17 ፤ በመካከልህ አልፋለሁና በወይኑ ቦታ ሁሉ ልቅሶ ይሆናል፥ ይላል እግዚአብሔር።
18 ፤ የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።
19 ፤ ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው።
20 ፤ የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?
21 ፤ ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ ተጸይፌውማለሁ፤ የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም።
22 ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም።
23 ፤ የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም።
24 ፤ ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ።
25 ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ በምድረ በዳ አርባ ዓመት ሙሉ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኛልን?
26 ፤ ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ምስሎች፥ የሞሎክን ድንኳንና የአምላካችሁን የሬፋን ኮከብ አነሣችሁ።
27 ፤ ስለዚህ ከደማስቆ ወደዚያ አስማርካችኋለሁ፥ ይላል ስሙ የሠራዊት አምላክ የተባለ እግዚአብሔር።