ትንቢተ አሞጽ

1 2 3 4 5 6 7 8 9


ምዕራፍ 4

በሰማርያ ተራራ የምትኖሩ፥ ድሆችንም የምትበድሉ፥ ችጋረኞችንም የምታሰጨንቁ፥ ጌቶቻቸውንም። አምጡ እንጠጣ የምትሉ እናንተ የባሳን ላሞች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ።
2 ፤ ጌታ እግዚአብሔር። እናንተን በሰልፍ ዕቃ፥ ቅሬታችሁንም በመቃጥን የሚወስዱበት ቀን፥ እነሆ፥ በላያችሁ ይመጣል ብሎ በቅዱስነቱ ምሎአል።
3 ፤ እያንዳንዳችሁ በየፊታችሁ በተነደለ ስፍራ ትወጣላችሁ፤ በሬማንም ትጣላላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
4 ፤ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህን ወድዳችኋልና ወደ ቤቴል ኑና ኃጢአትን ሥሩ፤ ወደ ጌልገላ ኑና ኃጢአትን አብዙ፤ በየማለዳውም መሥዋዕታችሁን፥ በየሦስተኛውም ቀን አሥራታችሁን አቅርቡ፤
5 ፤ እርሾ ካለበትም የምስጋናውን መሥዋዕት አቅርቡ፥ በፈቃዳችሁም የምታቀርቡትን አውጁና አውሩ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
6 ፤ በከተማችሁ ሁሉ ጥርስን ማጥራት፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣት ሰጠኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
7 ፤ መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብ ከለከልኋችሁ፤ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፥ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ በአንድ ወገን ዘነበ፥ ያልዘነበበትም ወገን ደረቀ።
8 ፤ የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች ወደ አንዲት ከተማ ወኃ ይጠጡ ዘንድ ሄዱ፥ ነገር ግን አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
9 ፤ በዋግና በአረማሞ መታኋችሁ፤ የአታክልቶቻችሁንም ብዛት ወይኖቻችሁንም በለሶቻችሁንም ወይራዎቻችሁንም ተምች በልቶአል፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
10 ፤ በግብጽ እንደ ነበረው ቸነፈርን ሰደድሁባችሁ፤ ጐበዛዝቶቻችሁን በሰይፍ ገደልሁ፥ ፈረሶቻችሁንም አስማረክሁ፤ የሰፈራችሁንም ግማት ወደ አፍንጫችሁ አወጣሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
11 ፤ ሰዶምንና ገሞራን እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ እንዲሁ ገለበጥኋችሁ፥ እናንተም ከእሳት ውስጥ እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ ነገር ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
12 ፤ ስለዚህ፥ እስራኤል ሆይ፥ እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እስራኤልም ሆይ፥ እንደዚህ ስለማደርግብህ አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ።
13 ፤ እነሆ፥ ተራሮችን የሠራ፥ ነፋስንም የፈጠረ፥ የልቡንም አሳብ ለሰው የሚነግር፥ ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፥ ስሙ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው።