ትንቢተ አሞጽ

1 2 3 4 5 6 7 8 9


ምዕራፍ 2

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የኤዶምያስን ንጉሥ አጥንት አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የሞዓብ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
2 ፤ በሞዓብ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የቂርዮትንም አዳራሾች ትበላለች፤ ሞዓብም በውካታና በጩኸት በመለከትም ድምፅ ይሞታል፤
3 ፤ ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፥ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
4 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉት ሐሰታቸው አስቶአቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የይሁዳ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
5 ፤ በይሁዳ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች።
6 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጻድቁን ስለ ብር፥ ችጋረኛውንም ስለ አንድ ጥንድ ጫማ ሽጠውታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የእስራኤል ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም።
7 ፤ የድሆችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፥ የትሑታንንም መንገድ ያጣምማሉ፤ ቅዱሱንም ስሜን ያረክሱ ዘንድ አባትና ልጁ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤
8 ፤ በመሠዊያውም ሁሉ አጠገብ ለመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ ይተኛሉ፤ በአምላካቸውም ቤት ውስጥ በካሣ የተወሰደውን ወይን ጠጅ ይጠጣሉ።
9 ፤ እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ኮምበል ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ።
10 ፤ የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፥ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ።
11 ፤ ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጐበዛዝቶቻችሁም ናዝራውያንን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህ እንደዚህ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር።
12 ፤ እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም። ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ አዘዛችኋቸው።
13 ፤ እነሆ፥ ነዶ የተሞላች ሰረገላ እንደምትደቀድቅ እንዲሁ እደቀድቃችኋለሁ።
14 ፤ ከርዋጪም ሽሽት ይጠፋል፥ ብርቱውም በብርታቱ አይበረታም፥ ኃያሉም ነፍሱን አያድንም፤
15 ፤ ቀስተኛውም አይቆምም፥ ፈጣኑም አይድንም፥ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤
16 ፤ በኃያላኑም መካከል ልበ ሙሉው በዚያ ቀን ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።