ትንቢተ አብድዩ

1


ምዕራፍ 1

የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ወሬ ሰምተናል፤ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ። ተነሡ፥ በላይዋም በሰልፍ እንነሣ ብሎአል።
2 ፤ እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፤ አንተ እጅግ ተንቀሃል።
3 ፤ በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም። ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል።
4 ፤ እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
5 ፤ ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን የሚሰርቁ አይደሉምን? ወይንንም የሚቈርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ አያስቀሩምን?
6 ፤ አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ! ዔሳው ምንኛ ተመረመረ! የተሸሸገበት ነገር ምንኛ ተፈለገ!
7 ፤ የተማማልሃቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፤ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፤ በበታችህም አሽክላ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም።
8 ፤ በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል እግዚአብሔር።
9 ፤ ቴማን ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በመገደል ይጠፉ ዘንድ ኃያላንህ ይደነግጣሉ።
10 ፤ በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ግፍ እፍረት ይከድንሃል፥ ለዘላለምም ትጠፋለህ።
11 ፤ በፊቱ አንጻር በቆምህ ቀን፥ አሕዛብ ጭፍራውን በማረኩበት፥ እንግዶችም በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተ ደግሞ ከእነርሱ እንደ አንዱ ነበርህ።
12 ፤ ነገር ግን በመከራው ቀን ወንድምህን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች ላይ ደስ ይልህ ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን በትዕቢት ትናገር ዘንድ አይገባህም ነበር።
13 ፤ በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር ትገባ ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ አይገባህም ነበር።
14 ፤ የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ትቆም ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ትሰጥ ዘንድ አይገባህም ነበር።
15 ፤ የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና፤ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል።
16 ፤ በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፤ አዎን ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ።
17 ፤ ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይሆናሉ፥ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፤ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ።
18 ፤ እግዚአብሔርም ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፤ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፤ ከዔሳውም ቤት ቅሬታ የለውም።
19 ፤ የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቈላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፤ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል።
20 ፤ ይህም የእስራኤል ልጆች የጭፍራቸው ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፤ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ።
21 ፤ በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፤ መንግሥቱም ለእግዚአብሔር ይሆናል።