መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 8

እግዚአብሔርም ኢያሱን። አትፍራ፥ አትደንግጥ፤ ሰልፈኞችን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ።
2 ፤ በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፤ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፤ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ አለው።
3 ፤ ኢያሱም ሰልፈኞቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፤ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥
4 ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፤ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ተዘጋጁ፤
5 ፤ እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፤
6 ፤ አስቀድመን እንደ ሸሸን የምንሸሽ ይመስላቸዋልና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፤ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን።
7 ፤ እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ።
8 ፤ በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፤ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጉ፤ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ።
9 ፤ ኢያሱም ሰደዳቸው፤ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፥ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በምዕራብ በኩል ተቀመጡ፤ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ።
10 ፤ ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ ሕዝቡንም አሰለፈ፤ እርሱም የእስራኤልም ሽማግሌዎች ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ።
11 ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ወጥተው ቀረቡ፥ ወደ ከተማይቱም ፊት ደረሱ፥ በጋይም በሰሜን በኩል ሰፈሩ፤ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ።
12 ፤ አምስት ሺህ ያህል ሰዎችንም ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በከተማይቱም በምዕራብ በኩል ደብቆ አስቀመጣቸው።
13 ፤ በከተማይቱ በሰሜን በኩል የነበሩትን ሠራዊት ሁሉ በከተማይቱም በምዕራብ በኩል የተደበቁትን ሕዝብ አኖሩ፤ ኢያሱም በዚያች ሌሊት ወደ ሸለቆው መካከል ሄደ።
14 ፤ የጋይም ንጉሥ ባየ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ቸኵለው በማለዳ ተነሡ፤ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ወዳለው ወደ አንድ ስፍራ እስራኤልን በሰልፍ ለመገናኘት ወጡ፤ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ግን ድብቅ ጦር እንዳለ አያውቅም ነበር።
15 ፤ ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ድል የተነሡ መስለው ከፊታቸው በምድረ በዳው መንገድ ሸሹ።
16 ፤ በከተማይቱም የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሊያሳድዱአቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም አሳደዱት፥ ከከተማይቱም እንዲርቁ አደረጓቸው።
17 ፤ በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፤ ከተማይቱንም ከፍተው ተዉ፥ እስራኤልንም አሳደዱት።
18 ፤ እግዚአብሔር ኢያሱን። ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በላይዋ ዘርጋ አለው፤ ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር በከተማይቱ ላይ ዘረጋ።
19 ፤ የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፥ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ሮጡ፥ ወደ ከተማይቱም ገብተው ያዙአት፤ ፈጥነውም ከተማይቱን በእሳት አቃጠሉአት።
20 ፤ የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፥ ወዲህና ወዲያም መሸሽ አልቻሉም፤ ወደ ምድረ በዳም የሸሹ ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ተመለሱ።
21 ፤ ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማይቱን እንደ ያዙ፥ የከተማይቱም ጢስ እንደ ተነሣ ባዩ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉ።
22 ፤ ሌሎቹም በላያቸው ከከተማይቱ ወጡ፤ የጋይም ሰዎች በእስራኤል መካከል ሆኑ፥ እስራኤልም ከበቡአቸው፤ አንድ እንኳ ሳይቀር ሳያመልጥም ገደሉአቸው።
23 ፤ የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።
24 ፤ እንዲህም ሆነ፤ እስራኤልን ሊያሳድዱ ሄደው የነበሩትን የጋይን ሰዎች ሁሉ በሜዳና በምድረ በዳ ከገደሉአቸው በኋላ፥ እነርሱም በሰይፍ ስለት እስኪያልቁ ድረስ ከወደቁ በኋላ፥ እስራኤል ሁሉ ወደ ጋይ ተመለሱ፥ በሰይፍም ስለት መቱአት።
25 ፤ በዚያም ቀን የወደቁት ሁሉ ወንድም ሴትም የጋይ ሰዎች ሁሉ አሥራ ሁለት ሺህ ነፍስ ነበሩ።
26 ፤ ኢያሱም በጋይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋባትን እጁን አላጠፈም።
27 ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ኢያሱን እንዳዘዘው ቃል የዚያችን ከተማ ከብትና ምርኮ እስራኤል ለራሳቸው ዘረፉ።
28 ፤ ኢያሱም ጋይን አቃጠላት፥ እስከ ዛሬም ድረስ ድብድባና በረሃ ለዘላለም አደረጋት።
29 ፤ የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ፀሐይም በገባች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ሬሳውንም ከዛፍ አወረዱት፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ጣሉት፥ በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት።
30 ፤ የዚያን ጊዜም ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ።
31 ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዘ፥ በሙሴም ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፥ መሠዊያው ካልተወቀረና ብረት ካልነካው ድንጋይ ነበረ፤ በእርሱም ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት ሠዉ።
32 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሲያዩ በዚያ ስፍራ በድንጋዮቹ ላይ የሙሴን ሕግ ጻፈባቸው።
33 ፤ የእስራኤልንም ሕዝብ አስቀድሞ ይባርኩ ዘንድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘ፥ እስራኤል ሁሉ፥ ሽማግሌዎቻቸውም፥ አለቆቻቸውም፥ ፈራጆቻቸውም፥ የአገሩ ልጆችም፥ መጻተኞችም፥ እኩሌቶቹ በገሪዛን ተራራ ፊት እኩሌቶቹም በጌባል ተራራ ፊት ሆነው፥ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በተሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት፥ በታቦቱም ፊት በወዲህና በወዲያ ቆመው ነበር።
34 ፤ ከዚህም በኋላ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ሁሉ፥ የሕጉን ቃሎች ሁሉ በረከቱንና እርግማኑን አነበበ።
35 ፤ ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶቹም በሕፃናቱም በመካከላቸውም በሚኖሩት መጻተኞች ፊት ሁሉን አነበበ እንጂ ሙሴ ካዘዘው አንዲት ቃል አላስቀረም።