መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 1

እንዲህም ሆነ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ።
3 ፤ ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ።
4 ፤ ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል።
5 ፤ በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም።
6 ፤ ለአባቶቻቸው። እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ።
7 ፤ ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።
8 ፤ የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።
9 ፤ በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ አይዞህ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?
10
11 ፤ ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች። በሰፈሩ መካከል እለፉ፥ ሕዝቡንም። አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር እስከ ሦስት ቀን ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ ብላችሁ እዘዙአቸው ብሎ አዘዘ።
12 ፤ ኢያሱም የሮቤልን ልጆች የጋድንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
13 ፤ የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስቡ። አምላካችሁ እግዚአብሔር ያሳርፋችኋል፥ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።
14 ፤ ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፤ ነገር ግን እናንተ፥ ጽኑዓን ኃያላን ሁሉ፥ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፥ እርዱአቸውም፥
15 ፤ እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፤ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በፀሐይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ ትወርሱአትማላችሁ።
16 ፤ እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት። ያዘዝኸንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ወደምትልከንም ስፍራ እንሄዳለን።
17 ፤ በሁሉም ለሙሴ እንደ ታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዛለን፤ ብቻ አምላክህ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን።
18 ፤ በትእዛዝህ የሚያምፅ ሁሉ የምታዝዘውንም ቃል ሁሉ የማይሰማ፥ እርሱ ይገደል፤ ብቻ ጽና፥ አይዞህ።