መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 13

ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አለው። አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፤ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፤
2 ፤ የቀረችውም ምድር ይህች ናት፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥
3 ፤ በግብፅ ፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥
4 ፤ በደቡብም በኩል የኤዋውያን፥ የከነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥
5 ፤ የጌባላውያውንም ምድር፥ በምሥራቅም በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥
6 ፤ በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፤ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፤ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ርስት አድርገህ አካፍላቸው።
7 ፤ አሁንም ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው።
8 ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንደ ሰጣቸው ከእርሱ ከምናሴ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ።
9 ፤ በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥
10 ፤ በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥
11 ፤ ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ዳርቻ ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥
12 ፤ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፤ እርሱም ከራፋይም የቀረ ነበረ፤ እነዚህንም ሙሴ መታቸው አወጣቸውም።
13 ፤ የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላወጡም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ።
14 ፤ ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር የቀረበው በእሳት የተደረገ መሥዋዕት ርስታቸው ነው፥ እርሱ እንደ ተናገራቸው።
15 ፤ ሙሴም ለሮቤል ልጆች ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው።
16 ፤ ድንበራቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ የሜድባ ሜዳ ሁሉ፥
17 ፤ ሐሴቦንም፥ በሜዳውም ያሉት ከተሞችዋ ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበኣል፥
18 ፤ ቤትበኣልምዖን፥ ያሀጽ፥ ቅዴሞት፥
19 ፤ ሜፍዓት፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ጼሬትሻሐር፥
20 ፤ ቤተ ፌጎር፥ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለው ምድር፥ ቤትየሺሞት፥
21 ፤ የሜዳውም ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፤ ሙሴም እርሱንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቆምን፥ ሱርን፥ ሑርን፥ ሪባን መታቸው።
22 ፤ ከገደሉአቸውም ሰዎች ጋር የእስራኤል ልጆች ምዋርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን በሰይፍ ገደሉት።
23 ፤ የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
24 ፤ ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው።
25 ፤ ድንበራቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በረባት ፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥
26 ፤ ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ ራማት ምጽጴ፥ እስከ ብጦኒም ድረስ፥ ከመሃናይም ጀምሮ እስከ ዳቤር ዳርቻ ድረስ፥
27 ፤ በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ቅሬታ ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኪኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበር።
28 ፤ የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
29 ፤ ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሰጣቸው፤ ለምናሴም ልጆች ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
30 ፤ ድንበራቸውም ከመሃናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥
31 ፤ በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስታሮትና ኤድራይ ነበረ። እነዚህም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ሆኑ፤ ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
32 ፤ ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የከፈለው ርስት ይህ ነው።
33 ፤ ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳላቸው ርስታቸው እርሱ ነው።