መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 5

እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል የነበሩት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ፥ በባሕሩም አጠገብ የነበሩ የከነዓናውያን ነገሥት ሁሉ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት የዮርዳኖስን ውኃ እስኪሻገሩት ድረስ እንዳደረቀ በሰሙ ጊዜ፥ ልባቸው ቀለጠ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ነፍስ ከዚያ ወዲያ አልቀረላቸውም።
2 ፤ በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ኢያሱን። የባልጩት መቍረጫ ሠርተህ የእስራኤልን ልጆች ሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው አለው።
3 ፤ ኢያሱም የባልጩት መቍረጫ ሠርቶ የግርዛት ኮረብታ በተባለ ስፍራ የእስራኤልን ልጆች ገረዘ።
4 ፤ ኢያሱ የገረዘበትም ምክንያት ይህ ነው፤ ከግብፅ የወጡት ሕዝብ ወንዶች ሰልፈኞች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞቱ።
5 ፤ የወጡት ሕዝብ ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ነገር ግን ከግብፅ በወጡበት መንገድ በምድረ በዳ የተወለዱት ሕዝብ ሁሉ አልተገረዙም ነበር።
6 ፤ እግዚአብሔርም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው የማለላቸው፥ ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርንም ቃል ያልሰሙ፥ እነዚያ ሰልፈኞች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር።
7 ፤ ልጆቻቸውን በእነርሱ ፋንታ አስነሣ፥ እነዚህንም ኢያሱ ገረዛቸው፤ በመንገድ ሳሉ ስላልገረዙአቸው ሸለፈታሞች ነበሩና።
8 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተገረዙ ጊዜ እስኪድኑ ድረስ በሰፈር ውስጥ በየስፍራቸው ተቀመጡ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን። ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ አለው፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ።
10 ፤ የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፤ ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በኢያሪኮ ሜዳ ፋሲካ አደረጉ።
11 ፤ ከፋሲካውም በኋላ በነጋው የምድሪቱን ፍሬ የቂጣ እንጎቻ ቆሎም በዚያው ቀን በሉ።
12 ፤ በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።
13 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ። ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው።
14 ፤ እርሱም። አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና። ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው።
15 ፤ የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን። አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ።