መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 6

ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርስዋ የሚገባ ከእርስዋም የሚወጣ ማንም አልነበረም።
2 ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው። ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ።
3 ፤ ሰልፈኞቻችሁ ሁሉ ከተማይቱን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ።
4 ፤ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ።
5 ፤ ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱንም ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ይገባባታል።
6 ፤ የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ። የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አላቸው።
7 ፤ ሕዝቡንም። ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ሰልፈኞችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አለ።
8 ፤ ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር።
9 ፤ ሰልፈኞቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የቀረውም ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር።
10 ፤ ኢያሱም ሕዝቡን። እኔ። ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታንሡ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ ብሎ አዘዛቸው።
11 ፤ እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ።
12 ፤ ኢያሱም ማለዳ ተነሣ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ።
13 ፤ ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ሰልፈኞቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር።
14 ፤ በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ።
15 ፤ በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፥ እንደዚህም ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ።
16 ፤ በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን አለ። እግዚአብሔር ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ።
17 ፤ ከተማይቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱ ረዓብ ከእርስዋም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ።
18 ፤ እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደ ሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁትማላችሁ።
19 ፤ ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።
20 ፤ ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ።
21 ፤ በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።
22 ፤ ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች። ወደ ጋለሞታይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ አላቸው።
23 ፤ ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው።
24 ፤ ከተማይቱንም በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አደረጉት።
25 ፤ ኢያሪኮን ሊሰልሉ ኢያሱ የሰደዳቸውንም መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተ ሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርስዋም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች።
26 ፤ በዚያን ጊዜም ኢያሱ። ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኵር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ ብሎ ማለ።
27 ፤ እግዚአብሔርም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ወጣ።