መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 22

በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው።
2 ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፤
3 ፤ ይህንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል።
4 ፤ አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ አሁን እንግዲህ ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ።
5 ፤ ብቻ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ።
6 ፤ ኢያሱም መረቃቸው፥ ሰደዳቸውም፤ ወደ ቤታቸውም ሄዱ።
7 ፤ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ ወገን በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው በሰደዳቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ መረቃቸው።
8 ፤ በብዙ ብልጥግና በእጅግም ብዙ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ በእጅግም ብዙ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።
9 ፤ የሮቤልም ልጆች የጋድም ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሄዱ፤ በሙሴም እጅ በተሰጠ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ተቀበሉአት ወደ ርስታቸው ወደ ገለዓድ ምድር ይገቡ ዘንድ በከነዓን ምድር ካለችው ከሴሎ ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ተመለሱ።
10 ፤ በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያም በመጡ ጊዜ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዚያ በዮርዳኖስ አጠገብ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ።
11 ፤ ለእስራኤልም ልጆች። እነሆ፥ በከነዓን ምድር ዳርቻ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው ግዛት፥ የእስራኤል ልጆች ባሉበት ወገን፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ መሠዊያ ሠርተዋል የሚል ወሬ ደረሰላቸው።
12 ፤ የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ወጥተው እነርሱን ሊዋጉ በሴሎ ተሰበሰቡ።
13 ፤ የእስራኤልም ልጆች በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ላኩ።
14 ፤ ከእርሱም ጋር አሥር አለቆች ነበሩ፥ ከእስራኤል ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ የአባቶች ቤት አለቃ፤ እያንዳንዱም በእስራኤል አእላፋት መካከል የእየአባቶቻቸው ቤት አለቃ ነበረ።
15 ፤ በገለዓድም ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ መጡ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩአቸው።
16 ፤ የእግዚአብሔር ማኅበር ሁሉ የሚለው ይህ ነው። ይህ በእስራኤል አምላክ ላይ ያደረጋችሁት ኃጢአት ምንድር ነው? ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋል፤ ዛሬም መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል።
17 ፤ እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሰፍት ወረደ።
18 ፤ እናንተ ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ትመለሳላችሁን? ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ ነገ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ይቈጣል።
19 ፤ ነገር ግን የርስታችሁ ምድር የረከሰ ቢመስላችሁ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደሚቀመጥበት ወደ እግዚአብሔር ርስት ምድር አልፋችሁ በመካከላችን ውረሱ፤ ከአምላካችንም ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለእናንተ መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔርና በእኛ ላይ አታምፁ።
20 ፤ የዛራ ልጅ አካን እርም ነገር በመውሰድ ኃጢአትን ስለ ሠራ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ቍጣ አልወረደምን? እርሱም በኃጢአቱ ብቻውን አልሞተም።
21 ፤ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል አእላፋት አለቆች እንዲህ ብለው መለሱላቸው።
22 ፤ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር፥ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር እርሱ አውቆታል፥ እስራኤልም ያውቀዋል፤ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀንና ተላልፈን እንደ ሆነ ዛሬ አታድነን፤
23 ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል እንድንመለስ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቍርባን እንድናሳርግበት፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት እንድናቀርብበት ብለን መሠዊያ ሠርተን እንደ ሆነ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ይበቀለን፤
24 ፤ ይልቁንም ከልባችን ፍርሃት የተነሣ። በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን። ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን አላችሁ?
25 ፤ እናንተ የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ እግዚአብሔር በእኛና በእናንተ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጎአልና በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም ይሉአቸዋል ብለን ይህን አደረግን። በዚህም ልጆቻችሁ ልጆቻችንን እግዚአብሔርን ከመፍራት አስተዋቸዋል።
26 ፤ ስለዚህም። መሠዊያ እንሥራ አልን፤ ነገር ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት አይደለም፤
27 ፤ ነገር ግን በእኛና በእናንተ መካከል ከእኛም በኋላ በትውልዳችንና በትውልዳችሁ መካከል በሚቃጠል መሥዋዕትና በቍርባን በደኅንነትም መሥዋዕታችን እግዚአብሔርን እናመልክ ዘንድ፥ በሚመጣውም ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን። በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም እንዳይሉ ምስክር ይሆናል።
28 ፤ ስለዚህም አልን። በሚመጣው ዘመን ለእኛ ወይም ለትውልዳችን ይህን ሲሉ፥ እኛ። እነሆ፥ አባቶቻችን ያደረጉትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ እዩ፤ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር ነው እንጂ ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት አይደለም እንላለን።
29 ፤ በማደሪያው ፊት ካለው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለእህል ቍርባን ለሌላ መሥዋዕትም የሚሆን መሠዊያን የሠራነው በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እግዚአብሔርንም ዛሬ መከተልን ለመተው በማለት እንደ ሆነ ይህ ከእኛ ይራቅ።
30 ፤ ካህኑ ፊንሐስና የማኅበሩ አለቆች፥ ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል አእላፋት አለቆች፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ልጆች የተናገሩትን ቃል በሰሙ ጊዜ ነገሩ እጅግ ደስ አሰኛቸው።
31 ፤ የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች ለምናሴም ልጆች። ይህን መተላለፍ በእግዚአብሔር ላይ አላደረጋችሁምና እግዚአብሔር በመካከላችን እንዳለ ዛሬ እናውቃለን፤ አሁን የእስራኤልን ልጆች ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል አላቸው።
32 ፤ የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና አለቆቹ ከሮቤል ልጆችና ከጋድ ልጆች ዘንድ ከገለዓድ አገር ወደ ከነዓን አገር ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ ወሬም አመጡላቸው።
33 ፤ ነገሩም የእስራኤልን ልጆች ደስ አሰኘ፤ የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን አመሰገኑ፥ ከዚያም ወዲያ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የተቀመጡባትን ምድር ያጠፉ ዘንድ ወጥተው እንዲወጉአቸው አልተናገሩም።
34 ፤ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም። እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆነ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው ሲሉ መሠዊያውን ምስክር ብለው ጠሩት።