የሉቃስ ወንጌል
ምዕራፍ 6
በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር።
2 ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ። በሰንበት ሊያደርግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው።
3 -
4 ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ። ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱ አብረውት ከነበሩ ጋር ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ከካህናት ብቻ በቀር መብላቱ ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ ይዞ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንደ ሰጣቸው ይህን አላነበባችሁምን? አለ።
5 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም።
6 በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤
7 ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር።
8 እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው። ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ።
9 ኢየሱስም። እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው።
10 ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን። እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች።
11 እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ።
12 በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ።
13 በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤
14 እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥
15 ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥
16 የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው።
17 ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤
18 ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤
19 ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።
20 እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው። እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።
21 እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና።
22 ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ።
23 እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና።
24 ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና።
25 እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ።
26 ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።
27 ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥
28 የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ።
29 ጕንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ስጠው፥ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ደግሞ አትከልክለው።
30 ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፥ ገንዘብህንም የሚወስድ እንዲመልስ አትጠይቀው።
31 ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።
32 የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና።
33 መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና።
34 እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ።
35 ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና።
36 አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።
37 አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ።
38 ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።
39 ምሳሌም አላቸው። ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን?
40 ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል።
41 በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?
42 በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን። ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
43 ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም።
44 ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም።
45 በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል።
46 ስለ ምን። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም?
47 ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ።
48 ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም።
49 ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።