ምዕራፍ 24

ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ።
2 ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥
3 ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም።
4 እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤
5 ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።
6 -
7 የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ።
8 -
9 ቃሎቹንም አሰቡ፥ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው።
10 ይህንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና የያዕቆብም እናት ማርያም ከእነርሱም ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ።
11 ይህም ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም።
12 ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ።
13 እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤
14 ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።
15 ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤
16 ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር።
17 እርሱም። እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው።
18 ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ። አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው።
19 እርሱም። ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤
20 እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው።
21 እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው።
22 ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤
23 ሥጋውንም ባጡ ጊዜ። ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር።
24 ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም።
25 እርሱም። እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤
26 ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው።
27 ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።
28 ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው።
29 እነርሱ። ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ።
30 ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤
31 ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።
32 እርስ በርሳቸውም። በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ።
33 -
34 በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም። ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው።
35 እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው።
36 ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።
37 ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው።
38 እርሱም። ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል?
39 እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።
40 ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው።
41 እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ። በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው።
42 እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤
43 ተቀብሎም በፊታቸው በላ።
44 እርሱም። ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።
45 በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤
46 እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥
47 በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።
48 እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።
49 እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።
50 እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው።
51 ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ።
52 እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥
53 ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።