የሉቃስ ወንጌል
ምዕራፍ 20
አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና።
2 እስኪ ንገረን፤ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? ብለው ተናገሩት።
3 መልሶም። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም ንገሩኝ፤
4 የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው።
5 እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤
6 ከሰው ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ ይወግሩናል፤ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉ ያምኑ ነበርና አሉ።
7 መልሰውም። ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት።
8 ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።
9 ይህንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይላቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ ለገበሬዎችም አከራይቶ ለብዙ ዘመን ወደ ሌላ አገር ሄደ።
10 በጊዜውም ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት።
11 ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት።
12 ጨምሮም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይህን ደግሞ አቍሰለው አወጡት።
13 የወይኑም አትክልት ጌታ። ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ።
14 ገበሬዎቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ።
15 ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል?
16 ይመጣል እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ይህንም በሰሙ ጊዜ። ይህስ አይሁን አሉ።
17 እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ። እንግዲህ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ ተብሎ የተጻፈው ይህ ምንድር ነው?
18 በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይፈጨዋል አለ።
19 የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት እጃቸውን ሊጭኑበት ፈለጉ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።
20 ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት።
21 ጠይቀውም። መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤
22 ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት።
23 እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ። ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤
24 መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም። የቄሣር ነው አሉት።
25 እርሱም። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።
26 በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።
27 ትንሣኤ ሙታንንም የሚክዱ ከሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ቀርበው ጠየቁት፥
28 እንዲህ ሲሉ። መምህር ሆይ፥ ሙሴ። ሚስት ያለችው የአንድ ሰው ወንድም ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን።
29 እንግዲያስ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የፊተኛውም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤
30 -
31 ሁለተኛውም አገባት፥ ሦስተኛውም፥ እንዲሁም ሰባቱ ደግሞ ልጅ ሳይተዉ ሞቱ።
32 ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች።
33 እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች?
34 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፥
35 ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥
36 ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።
37 ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤
38 ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
39 ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው። መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ አሉት።
40 ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም።
41 እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?
42 -
43 ዳዊትም ራሱ በመዝሙራት መጽሐፍ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ይላል።
44 እንግዲህ ዳዊት። ጌታ ብሎ ይጠራዋል፥ እንዴትስ ልጁ ይሆናል?
45 ሕዝቡም ሁሉ ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን።
46 ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤
47 የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ።