የሉቃስ ወንጌል
ምዕራፍ 4
ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥
2 አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ።
3 ዲያብሎስም። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ። እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው።
4 ኢየሱስም። ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት።
5 ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው።
6 ዲያብሎስም። ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤
7 ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው።
8 ኢየሱስም መልሶ። ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው።
9 -
10
11 ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቁሞ። ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፥ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።
12 ኢየሱስም መልሶ። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል አለው።
13 ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ።
14 ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ።
15 እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።
16 ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ።
17 -
18
19 የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።
20 መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር።
21 እርሱም። ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር።
22 ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ። ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር።
23 እርሱም። ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ። ባለ መድኃኒት ሆይ፥ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ ትሉኛላችሁ አላቸው።
24 እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ነቢይ በገዛ አገሩ ከቶ አይወደድም።
25 ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፥ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ በምድር ሁሉ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤
26 ኤልያስም በሲዶና አገር ወዳለች ወደ ሰራፕታ ወደ አንዲት መበለት እንጂ ከእነርሱ ወደ አንዲቱ አልተላከም።
27 በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፥ ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልነጻም።
28 በምኵራብም የነበሩ ሁሉ ይህን ሰምተው ቍጣ ሞላባቸው፥ ተነሥተውም ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፥
29 ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤
30 እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
31 ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤
32 ቃሉ በሥልጣን ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ።
33 በምኵራብም የርኵስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኾ።
34 ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ።
35 ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ።
36 ሁሉንም መደነቅ ያዛቸው፥ እርስ በርሳቸውም። ይህ ቃል ምንድር ነው? በሥልጣንና በኃይል ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛልና፥ ይወጡማል ብለው ተነጋገሩ።
37 ዝናም በዙሪያው ባለች አገር ወደ ስፍራው ሁሉ ስለ እርሱ ወጣ።
38 በምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ንዳድ ታማ ነበር ስለ እርስዋም ለመኑት።
39 በአጠገብዋም ቆሞ ንዳዱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ያንጊዜውንም ተነሥታ አገለገለቻቸው።
40 ፀሐይም በገባ ጊዜ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ እርሱም በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው።
41 አጋንንትም ደግሞ። አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮኹም ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ ገሠጻቸውም ክርስቶስም እንደ ሆነ አውቀውት ነበርና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።
42 በጸባም ጊዜ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፥ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ወደዱ።
43 እርሱ ግን። ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል አላቸው።
44 በገሊላም ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።