የሉቃስ ወንጌል
ምዕራፍ 12
በዚያን ጊዜ የሕዝብ አእላፍ እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ተሰብስበው ሳሉ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር። አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው።
2 ነገር ግን የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም።
3 ስለዚህ በጨለማ የምትናገሩት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፥ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይሰበካል።
4 ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፥ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ።
5 እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ፥ እርሱን ፍሩ።
6 አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም።
7 ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።
8 እላችሁማለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤
9 በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል።
10 በሰው ልጅም ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሰድብ ግን አይሰረይለትም።
11 ወደ ምኵራቦችና ወደ መኳንንቶችም ወደ ገዢዎችም ሲጐትቱአችሁ፥ እንዴት ወይም ምን እንድትመልሱ ወይም እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
12 መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።
13 ከሕዝቡም አንድ ሰው። መምህር ሆይ፥ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው አለው።
14 እርሱም። አንተ ሰው፥ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ አንድሆን ማን ሾመኝ? አለው።
15 የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው።
16 ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል። አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት።
17 እርሱም። ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።
18 እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤
19 ነፍሴንም። አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ።
20 እግዚአብሔር ግን። አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው።
21 ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።
22 ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ።
23 ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና።
24 ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፥ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፥ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ?
25 ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?
26 እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ?
27 አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም።
28 እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?
29 እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤
30 ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል።
31 ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
32 አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።
33 ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤
34 መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።
35 ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤
36 እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ
37 ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል።
38 ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው።
39 ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር።
40 እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።
41 ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን? አለው።
42 ጌታም አለ። እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው?
43 ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው።
44 እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።
45 ያ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥
46 የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል።
47 የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤
48 ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።
49 በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ?
50 ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፥ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?
51 በምድር ላይ ሰላምንም ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፥ መለያየትን እንጂ።
52 ከአሁን ጀምሮ በአንዲት ቤት አምስት ሰዎች ይኖራሉና፤ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ሁለቱም በሦስቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።
53 አባት በልጁ ላይ ልጅም በአባቱ ላይ፥ እናት በልጅዋ ላይ ልጅዋም በእናትዋ ላይ፥ አማት በምራትዋ ላይ ምራትም በአማትዋ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።
54 ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ። ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው። ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፥ እንዲሁም ይሆናል፤
55 በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ። ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፥ ይሆንማል።
56 እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው?
57 ራሳችሁ ደግሞ ጽድቅን የማትፈርዱ ስለ ምን ነው?
58 ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ እንድትታረቅ ትጋ።
59 እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።