ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 8

የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፥ በታላቅም ቍጣ ስለ እርስዋ ቀንቻለሁ።
3 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል።
4 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል።
5 ፤ የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።
6 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ወራት በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ዓይን ዘንድ ድንቅ ቢሆን፥ በውኑ በእኔ ዓይን ዘንድ ደግሞ ድንቅ ይሆናልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
7 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከምዕራብ ምድር አድነዋለሁ፤
8 ፤ አመጣቸዋለሁም፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ይኖራሉ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ።
9 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መቅደሱ ይሠራ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ እናንተ ሆይ፥ እጃችሁን አበርቱ።
10 ፤ ከዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰውና ለእንስሳ ዋጋ አልነበረምና፤ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ነበርና ከአስጨናቂው የተነሣ ለሚገባውና ለሚወጣው ሰላም አልነበረም።
11 ፤ አሁን ግን እንደ ቀደመው ዘመን በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ላይ አልሆንም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
12 ፤ ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፤ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ።
13 ፤ የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ።
14 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብሁ፥ እንዳልተጸጸትሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥
15 ፤ እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ፤ አትፍሩ።
16 ፤ የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤
17 ፤ ሁላችሁም በባልንጀራችሁ ላይ ክፉን ነገር በልባችሁ አታስቡ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
18 ፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
19 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።
20 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ ከተሞች የሚቀመጡ አሕዛብ ገና ይመጣሉ፤
21 ፤ በአንዲትም ከተማ የሚኖሩ ሰዎች። እግዚአብሔርን እንለምን ዘንድ፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን እንፈልግ ዘንድ ኑ እንሂድ፤ እኔም እሄዳለሁ እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ።
22 ፤ ብዙ ወገኖችና ኃይለኞች አሕዛብ በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርንም ይለምኑ ዘንድ ይመጣሉ።
23 ፤ የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።