ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 2

ዓይኖቼንም አነሣሁ፤ እነሆም፥ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰውን አየሁ።
2 ፤ እኔም። አንተ ወዴት ትሄዳለህ? አልሁ። እርሱም። የኢየሩሳሌምን ወርድና ርዝመት ስንት መሆኑን ሰፍሬ አይ ዘንድ እሄዳለሁ አለኝ።
3 ፤ እነሆም፥ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፥ ሌላም መልአክ ሊገናኘው ወጣ፥
4 ፤ እንዲህም አለው። ሩጥ፥ ይህንም ጕልማሳ እንዲህ በለው። ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ሆና ትኖራለች።
5 ፤ እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በውስጥዋም ክብርን እሆናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
6 ፤ እናንተ ሆይ፥ ከሰሜን ምድር ሽሹ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እንደ አራቱ የሰማይ ነፍሳት በትኛችኋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
7 ፤ አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ኰብልዪ።
8 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ ልኮኛል፤ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና።
9 ፤ እነሆ፥ እጄን በላያቸው አወዛውዛለሁ፥ ተገዝተው ለነበሩት ብዝበዛ ይሆናሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
10 ፤ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁና ዘምሪ ደስም ይበልሽ፥ ይላል እግዚአብሔር።
11 ፤ በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፤ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ።
12 ፤ እግዚአብሔርም ይሁዳን እድል ፈንታው አድርጎ በተቀደሰችው ምድር ይወርሰዋል፥ ኢየሩሳሌምንም ዳግመኛ ይመርጣል።
13 ፤ እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ነቅቶአልና ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፥ በፊቱ ዝም በል።