ትንቢተ ዘካርያስ
ምዕራፍ 13
በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ከኃጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል።
2 ፤ በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ።
3 ፤ ማንም ደግሞ ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ። አንተ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም ይሉታል፤ ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባቱና እናቱ ይወጉታል።
4 ፤ በዚያም ቀን ነቢያቱ ሁሉ ትንቢትን ሲናገሩ እያንዳንዱ ስለ ራእዩ ያፍራል፤ ያታልሉም ዘንድ የማቅ ልብስ አይለብሱም።
5 ፤ እርሱ ግን። ከታናሽነቴ ጀምሮ ባሪያ ሆኜ ነበርሁና ገበሬ ሰው ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም ይላል።
6 ፤ ሰውም። ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቍስል ምንድር ነው? ይለዋል። እርሱም። በወዳጆቼ ቤት የቈሰልሁት ቍስል ነው ይላል።
7 ፤ ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ።
8 ፤ በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ክፍል ተቈርጠው ይሞታሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሦስተኛውም ክፍል በእርስዋ ውስጥ ይቀራል።
9 ፤ ሦስተኛውንም ክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም። ይህ ሕዝቤ ነው እላለሁ፤ እርሱም። እግዚአብሔር አምላኬ ነው ይላል።