ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 4

ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው አነቃኝ።
2 ፤ እርሱም። የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። እነሆ፥ ሁለንተናው ወርቅ የሆነውን መቅረዝ አየሁ፤ የዘይትም ማሰሮ በራሱ ላይ ነበረ፥ ሰባትም መብራቶች ነበሩበት፤ በራሱም ላይ ለነበሩት መብራቶች ሰባት ቧንቧዎች ነበሩአቸው።
3 ፤ ሁለት የወይራ ዛፎች፥ አንዱ በማሰሮው በስተ ቀኝ አንዱም በስተ ግራው ሆነው፥ በአጠገቡ ነበሩ አልሁ።
4 ፤ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት።
5 ፤ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውም መልአክ መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁ።
6 ፤ መልሶም። ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
7 ፤ ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም። ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል ብሎ ተናገረኝ።
8 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
9 ፤ የዘሩባቤል እጆች ይህን ቤት መሠረቱ፥ የእርሱም እጆች ይፈጽሙታል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
10 ፤ የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? እነዚህ ሰባቱ ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ እነዚህም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸው።
11 ፤ እኔም መልሼ። በመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉ እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድር ናቸው? አልሁት።
12 ፤ ሁለተኛም መልሼ። በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ ሆነው የወርቁን ዘይት የሚያፈስሱ እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድር ናቸው? አልሁት።
13 ፤ እርሱም መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም ። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁት።
14 ፤ እርሱም። በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ የተቀቡት እነዚህ ናቸው አለኝ።